
አዲስ አበባ: ጥር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን እና የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ተወላጅ ባለሀብቶች በአካባቢያቸው የልማት እና የሰላም ጉዳይ ላይ በአዲስ አበባ እየመከሩ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የደቡብ ጎንደር ዞን እና የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ተወላጅ ባለሃብቶች በደቡብ ጎንደር ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ እና በአካባቢው ያለውን ፀጋም በመጠቀም ወደልማት ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ነው እየመከሩ ይገኛሉ። ባለሀብቶቹ በተለይም በአካባቢው የተከሰተውን የጸጥታ መደፍረስ ችግር በጋራ ጥረት ወደ ሰላም ለመመለስ፣ በሚሠራው ሥራም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ግንዛቤ ለመፍጠር እና አብሮ ለመሥራት ያለመ ምክክር ነው እያካሄዱ የሚገኙት።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮነን ደቡብ ጎንደርም ኾነ ደብረታቦር ከተማ ሙሉ ፀጋን የተላበሰ ለልማት ምቹ የኾነ አካባቢ መኾኑን ተናግረዋል።
የአካባቢው ተወላጆች በሚሠራው የሰላም እና የልማት ሥራዎች ከጎናቸው በመኾን አብረዋቸው እንዲሠሩ ጠይቀዋል። አካባቢውም የሚጠበቅበትን ዝግጅት በማድረግ ባለሀብቶችን እየጠበቀ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
በመድረኩ የደብረታቦር ከተማ የኢንቨስትመንት ኮሚቴ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን እና የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር የሕዝብ ተመራጮች እና የፌዴራል የልዩ ልዩ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል
መድረኩ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ፣ ሌሎች የልማት ሥራዎችን ለመሥራት፣ በአካባቢው የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ ወደቀድሞው ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ እንደሚያስችል ተስፋ የተጣለበት ነው ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
