
ባሕርዳር: ጥር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከበይነመረብ ማኅበረሰብ እና ከዊንጉ አፍሪካ ጋር በመተባበር በአፍሪካ ኢጋድ ሀገራት የኢንተርኔት ስነ ምህዳር መሠረት ለመጣል የሚያስችል ለቀናት ሲካሄድ የነበረው የኢንተርኔት ልማት ኮንፈረንስ ተጠናቅቋል።
በኮንፍረንሱ የመዝግያ ሥነ ሥርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን ዓለማየሁ (ዶ.ር) በሀገራቱ መካከል የኢንተርኔት መለዋወጫ ነጥቦችን ተደራሽነትን ከማስፋፋት ጀምሮ የማኅበረሰብ ኔትዎርክ ዕድገት ባልተሟሉ አካባቢዎች ሀብታችንን እና ዕውቀታችንን በመጠቀም አዳዲስ ውጤቶችን ማስመዝገብ ይገባናል ብለዋል።
የ2025 የኢንተርኔት ልማት ኮንፈረንስ በኢጋድ ሀገራት የኢንተርኔት የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታትና አዳዲስ መፍትሔችን ለመተግበር የሚያስችል መኾኑንም አመላክተዋል። የአፍሪካ አህጉራዊ የነጻ ንግድ ስምምነትን ለመደገፍ አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከር አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል። በኢጋድ ሀገራት በጋራ ፖሊሲዎችንና ቴክኒካዊ ማዕቀፎችን ማውጣት ከድንበር በላይ በኾኑ የዲጂታል መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስትመንቶችን ለማሳደግ ያግዛል ነው ያሉት።
የኢጋድ ሀገራት በጋራ እድል ድንበር የማይገድበው ፈጠራን መጠቀም እንደሚገባቸውም ተገልጿል። ቀጣናው በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፋና ኾኖ የሚታይበትን እና የላቁ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ወቅቱ የሚሻውና ወደ ተግባር መግባት አስገዳጅ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ በኢጋድ ሀገራት የዲጂታል ኢኮኖሚ ዕድገትን ከማፋጠን ባለፈ በዓለም አቀፍ የዲጂታል ገበያ ግንባር ቀደም ተዋናይ ለመኾን መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል። በዘርፉ ድንበር ተሻጋሪ የዕውቀት መጋራትን አቅም ለማጎልበት እና የመሠረተ ልማት ተግዳሮቶችን ለመፍታት ግንኙነትን እና ትብብርን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል።
ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ለቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው በኢንተርኔት ልማት ኮንፈረንስ የተፈጠሩት ውይይቶች እና ስምምነቶች ስኬታማና ለተግባር የሚያነሳሱ እንደነበሩ ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
