
ደብረ ማርቆስ: ጥር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር “የወጣቶች ሚና ለዘላቂ አንድነትና አብሮነት” በሚል መሪ መልዕክት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሚሰጡ ወጣቶች የሥራ ማስጀመሪያ ሥልጠና ተሰጥቷል። በሥልጠና መርሐ ግብሩ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ አበባው ግዛቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭ ወጣቶች ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ እና አብሮነት እንዲጠናከር የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሰላም ሚኒስቴር የበጎ ፈቃድ ሥልጠና ክፍል ረዳት አሠልጣኝ ታጠቅ ቸኮል ሥልጠናው ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያለመ ነው ብለዋል። ረዳት አሠልጣኙ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት ከኅብረተሰቡ ጋር ይበልጥ ተቀራርበው ስለሚሠሩ ችግሮችን በማውጣት ሰላምን ለማስፈን ሰፊ እድል እንደሚያገኙም አስገንዝበዋል።
የደብረማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ተስፋዬ አዕምሮ በከተማ አሥተዳደሩ ውስጥ 400 ድንበር ተሻጋሪ ወጣቶችን የተለያዩ ሥልጠናዎች በመስጠት በሀገር አቀፍ ደረጃ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን እንዲሰጡ እየተሠራ ነው ብለዋል። የሥልጠናው ተሳታፊ ወጣቶችም በከተማ አሥተዳደሩ ውስጥ ረዳት የሌላቸውን ወገኖች የማገዝ ሥራ ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም ለወጣቶች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን በመስጠት በክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ወደ ቀደመ ሰላሙ ለመመለስ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል። በከተማ አሥተዳደሩ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ 200 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች በሥልጠናው ተሳትፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
