የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የበይነ መረብ የግብይት ሥርዓትን አስጀመረ።

292

አዲስ አበባ: ጥር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ይህ የበይነ መረብ የግብይት ሥርዓት የተለያዩ ሻጮች ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡበት እና የሚሳተፉበት ኾኖ ሸማቾች በግብይቱ ጨረታ ተሳታፊ በመኾን አሸናፊ የኾነው ሸማች ግብይት የሚፈፅምበት ሥርዓት ነው። በመድረኩ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ወንድማገኘሁ ነገራ የበይነ መረብ የግብይት ሥርዓት ተገበያዮች ካሉበት ኾነው መግዛት እና መሸጥ የሚችሉበትን ዕድል የሚፈጥር ቀላል አማራጭ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምርት ጥራትን በማስጠበቅ፣ ብክነትን በመከላከል፣ የገበያ አማራጮችን እና የምርት ብዝኀነትን በማስፋት ለሀገራችን ኢኮኖሚ አይተኬ ሚና ሲጫወት ቆይቷል ነው ያሉት። በዚህም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ተሞክሮ ለማካፈል ችለናል ሲሉ ተናግረዋል። የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን ዕውን ለማድረግ የበይነ መረብ የግብይት ሥርዓት አስተዋፅኦው ከፍተኛ እንደኾነ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ላለፉት 17 ዓመታት ሲጠቀምበት የቆየውን ሎጎ በአዲስ መቀየሩንም አሳውቋል። የንግዱን ዘርፍ ለማሳለጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ የተናገሩት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) በዚህም ተስፋ ሰጪ ስኬቶች እየተመዘገቡበት እንደኾነ አንስተዋል። የግብይት ሥርዓቱንም የማዘመን ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በዚሁ ዕለት በሁለት ዓመት ውስጥ ተገንብቶ የሚጠናቀቅ የባለ 24 ወለል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሕንፃ ማስጀመሪያ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

ዘጋቢ:- ቤቴል መኮንን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የአፈር እቀባ ሥራ ይሠራል “የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ”
Next article” ኢትዮጵያ ለምታደርገው የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር አቅም ያለው የሰው ኀይል ያስፈልጋል” በለጠ ሞላ (ዶ.ር)