
ጎንደር: ጥር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ላይ አርማጭሆ ወረዳ የ2017 ዓ.ም የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ሥራ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል። በአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራ ላይ ያገኘናቸው የወረዳው አርሶ አደሮች ባለፉት ዓመታት በሠሩት የእርከን ሥራ ሰብላቸው በጎርፍ እንዳይሸረሸር እንዳገዛቸው አስታውሰዋል።
የተፋሰስ ሥራው ለአፈር ለምነት ትልቅ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል። የላይ አርማጭሆ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አስረሳው ደሴ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ አፈርን ከክለት በመከላከል የተፈጥሮ ሚዛንን በማስጠበቅ እና ውኃን በማጎልበት ምርት እና ምርታማነትን እያሳደገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የወረዳው የኅብረተሰብ ክፍሎች የአፈር ጥበቃ ሥራ ጠቀሜታውን በመረዳታቸው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ነው ብለዋል። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ንጉሴ ማለደ የተሠሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ኅብረተሰቡ ባለቤት ኾኖ እንዲጠብቃቸው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል።
ባለፈው ዓመት ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የተፋሰስ ሥራ መሠራቱን ያስታወሱት አቶ ንጉሴ በዘንድሮው ዓመትም ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የተፋሰስ ልማቶች ይሠራሉ ብለዋል። ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ጎን ለጎን መደበኛ የሰላም እና የጸጥታ ሥራዎችን አቀናጅቶ መፈጸም እንደሚገባ ያነሱት ደግሞ የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የመሬት መምሪያ ኀላፊ አላምረው አበራ ናቸው።
የተሠሩ የተፈጥሮ ሀብት ሥራዎች የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ የክትትል እና ቁጥጥር ተግባራት ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
