
ባሕር ዳር: ጥር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያና የፓኪስታን እስላማዊ ሪፐብሊክ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የሚስችል የፖለቲካ ምክክር መግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱ በዓለምአቀፍ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ነው ተብሏል።ስምምነቱን የፈረሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የእና የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ተቀዳሚ ምክትል ሚኒስትር አምባሳደር ሀሚድ አሽገር ከሃን ናቸው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ግንኙነት በግብርና፣ ኢንቨስትመንት፣በንግድ፣በአቪዬሽን፣በኢንዱስትሪ፣በሳይንስእና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸዋል። የተፈረመው ስምምነት ሁለቱ ሀገራት በደቡብ ደቡብ ትብብር፣ በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸው መኾኑን ተናግረዋል።
የፓኪስታን ተቀዳሚ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀሚድ አሽገር ከሃን የኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ግንኙነት በሁሉም ዘርፎች እየተጠናከረ መምጣቱን አመላክተዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ጸጥታ እንዲረጋገጥ እያደረገች ያለውን ጥረትም አድንቀዋል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረችው እ.ኤ.አ.በ1958 ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
