ሕገ ወጥነትን በመከላከል የኑሮ ውድነትን ለመከላከል እየተሠራ መኾኑ ተጠቆመ።

42

ባሕር ዳር: ጥር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምርት እና ግብይት፣ የገበያ አረጋጊ፣ የሕገ ወጥ እና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ጥምር ግብረ ኀይል የወንጀል ጉዳዮች ክትትል ቴክኒክ ኮሚቴ በ2017 የግማሽ በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና በወንጀል የገንዘብ ቅጣት አወሳሰን እና አሰባሰብ ላይ እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ውይይት ተካሄዷል።

በውይይቱ ላይ የቴክኒክ ኮሚቴው፣ የክልል እና የፌደራል አባል ተቋማት መሪዎች እና የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። በመድረኩ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም የቴክኒክ ኮሚቴው የኢኮኖሚ ወንጀሎችን በተደራጀ እና በተቀናጀ አግባብ ለመከታተል፣ ለመቆጣጠር እና ሥርዓት ለማስያዝ የተቋቋመ ነው ብለዋል።

ኮሚቴው 13 የክልል እና የፌደራል አባል ተቋማት እንዳሉትም ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ ወንጀል ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ
👉 በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣
👉 ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት፣
👉 የአደገኛ እፆች ዝውውር፣
👉 ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣
👉 ከታክስ እና ጉምሩክ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች፣
👉ከንግድ ውድድር እና ሸማቾች መብት ጋር የተገናኘ ወንጀል እና
👉 ከንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ጠቅሰዋል።

የኢኮኖሚ ወንጀሎች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ እና ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ ሀብቶችን የሚቀሙ ናቸው ብለዋል። ወንጀሎች የሀገርን የኢኮኖሚ ሥርዓት እንደሚያዛቡም ቢሮ ኀላፊው አስገንዝበዋል። የምርት እና ግብይት፣ የገበያ አረጋጊ፣ የሕገ ወጥ እና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ጥምር ግብረ ኀይል የወንጀል ጉዳዮች ክትትል ቴክኒክ ኮሚቴ እነዚህን ትልልቅ ወንጀሎች የመከላከል፣ የመቆጣጠር እና ሥርዓት የማስያዝ ኀላፊነት ወስዶ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የቴክኒክ ኮሚቴው እንደሀገር የተወሰደውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ባልተገባ መንገድ ለመጠቀም የሚደረገውን እንቅስቃሴ ፈጥኖ የመቀልበስ ሥራ እየሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። ሕገ ወጥነት ሕጋዊ ሥርዓት እንዲይዝ በኀላፊነት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) የማክሮ ኢኮኖሚ መተግበርን ተከትሎ በክልሉ ላይ የኑሮ ውድነት እንዳይፈጠር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም የሕገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ንዑስ ኮሚቴ ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል። በተለይም የጸጥታ ችግሩ የፈጠረውን ተጨማሪ ተጽእኖ ለመከላከል በቁርጠኝነት እየተሠራ ነው ብለዋል። የጸጥታ ችግሩን ተከትሎ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ አካላት በብዛት ተስተውለዋል፤ ይህንንም ለማረም መጠነ ሰፊ ክትትል እና ቁጥጥር ተደርጓል ነው ያሉት ዶክተር ኢብራሂም።

በሕገ ወጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው የተገኙትን በመያዝ እና ግንዛቤ በመፍጠር ወደ ሕጋዊ የንግድ ሰንሰለት እንዲገቡ ተደርጓል። በተለይም በነዳጅ ምርቶች ላይ የታየው ሕገ ወጥ ዝውውር የሕዝቡን ኑሮ የፈተነ ነው ብለዋል ቢሮ ኀላፊው። ይህንን ለመቆጣጠር እና መልክ ለማስያዝ ጠንካራ የቁጥጥር ሥራ ተሠርቷል፤ የማደያ ባለቤቶችን እና አዘዋዋሪዎችን ጭምር በመያዝ ርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት።

ከ250 ሺህ ሊትር ነዳጅ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ጭምር በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቅሰዋል። ሕገ ወጥነትን በመከላከሉ ረገድ ኅብረተሰቡ ግንባር ቀደም ተባባሪ መኾን እንዳለበትም አሳስበዋል። የገቢዎች ሚኒስቴር የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አበረ አስፋው የአንድ ሀገረ መንግሥት የዜጎቹን ሁሉን አቀፍ ፍላጎቶች እና ጥያቄዎችን የመፍታት ቀዳሚ ኀላፊነት አለበት፤ ለዚህ ደግሞ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ማስፋት ግድ ይላል ብለዋል።

ለጠቅላላው ኅብረተሰብ ጥቅም ሲባል የሚወጡ ወጭዎችን ለመሸፈን ውጤታማ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት መኖር አለበትም ብለዋል። በታክስ ሕጎች አተገባበር ጉዳይ ላይ አስቀድሞ ተገቢ ግንዛቤ መፈጠር ውጤታማ ገቢ ለመሰብሰብ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል። የታክስ ባለሥልጣናት የታክስ አሥተዳደር ተገማችነትን በሚያረጋግጥ ኹኔታ ኀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ዳይሬክተሩ የሀገርን ገቢ ከሚቀንሱ ጉዳዮች መካከል የታክስ ወንጀል አንዱ መኾኑን አንስተዋል። በተለይም የታክስ ስወራ በተለያየ መልኩ የሚፈጸም አስቸጋሪ ወንጀል ስለመኾኑ ገልጸዋል። ይህንን ወንጀል ለመከላከል በአሠራር የላቀ የታክስ ሥርዓት እና ሕግ እየተዘረጋ ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለዜጎች በቂ እና ንጹህ የመጠጥ ውኃን ለማዳረስ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው” የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር
Next articleኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ባለብዙ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።