
ባሕር ዳር: ጥር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከ216 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ የሚገነባው በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አሥተዳደር ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ የጉላ ጅሮታ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል። በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር ኢ.ር) እና የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ/ር)ን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተውበታል።
ፕሮጀክቱ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚገነባ ሲኾን በሰከንድ 30 ሊትር ውኃ ማምረት የሚችል ነው ተብሏል። ግንባታው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት የሚሰጥ እና የማኅበረሰቡን የውኃ ይገንባልን ጥያቄ መመለስ እንደሚችል ይጠበቃል። ግንባታው ሲጠናቀቅ ከ25 ሺህ በላይ የሚኾን የማኅበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግም ይሆናል።
ግንባታው ሲጠናቀቅ ለመጭዎቹ 15 ዓመታት ማኅበረሰቡን በዘላቂነት የሚያገለግል ሲኾን የአካባቢውን የውኃ ሽፋን ከነበረበት 43 ነጥብ 45 በመቶ ወደ 58 ነጥብ 49 በመቶ የሚያሳድገው ይሆናል። የጉላ ጅሮታ እና አካባቢው ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም በአካባቢው የውኃ ችግር መኖሩን ገልጸው ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የነበረውን የውኃ እጥረት እንደሚፈታ ትልቅ ተስፋ አለን ብለዋል፡፡
በዚህም ደስተኞች ነን፤ ለግንባታው ስኬታማነት የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁዎች ነን ሲሉም ተደምጠዋል። በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የተገኙት ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር ) በሁለተኛው የንጹህ መጠጥ ውኃ እና ሳኒቴሽን ፕሮግራም ለዜጎች በቂ እና ንጹህ የመጠጥ ውኃን ለማዳረስ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በፕሮግራሙ እንደ ሀገር በታቀደው ልክ እየሠራን ነው ያሉት ሚኒስትሩ የጉላ ጅሮታ ፕሮጀክትም በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሠጥ በትኩረት ይሠራል ብለዋል። የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በድርቅ ምክንያት ለውኃ እጥረት ተጋላጭ የኾነውን የአካባቢው ማኅበረሰብ የመጠጥ ውኃ ችግር የሚፈታ እንደኾነ ገልጸዋል።
ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እና ጥራት ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትልም እናደርጋለን ብለዋል፡፡ ቢሮው በክልሉ የውኃ ተደራሽነትን ለማሳደግ በትጋት እየሠራ ነው፤ ተግባሩ ይበልጥ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይኾናል ሲሉም አክለዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
