
አዲስ አበባ: ጥር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጤና ሚኒስቴር “ማኅበራዊ ተጠያቂነት ለጤና አገልግሎት ጥራት እና ፍትሐዊ ተደራሽነት!” በሚል መሪ መልዕክት ሀገር አቀፋዊ የጤናው ዘርፍ የማኅበራዊ ተጠያቂነት ስትራቴጂ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ አስጀምሯል፡፡ በመርሐ ግብሩ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ መቅደስ ዳባ (ዶ.ር) በጤናው ዘርፍ የኅብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ለሟሟላት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት መንግሥት እና መንግሥታዊ ካልኾኑ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተሻለ የጤና አገልግሎት መስጠት መቻሉን ሚኒስትሯ አስታውሰዋል። በዚህም የጨቅላ ህጻናትን እና የእናቶችን የሞት ምጣኔ ከመቀነስ በተጨማሪ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት።
በተለይም በመጀመሪያ ደረጃ እና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ሕዝቡ የሚፈልገውን የጤና አገልግሎት ለመሥጠት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል። ይሁን እንጅ በጤና ተቋማት በሽታን መከላከል ብቻ ሳይኾን አክሞ የማዳን አቅምን ለማሳደግ ከዚህ በበለጠ በትኩረት መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል።
በጤና ተቋማት የአገልግሎት ጥራት እና ፍትሐዊ ተደራሽነት እንዲኖር ደግሞ የማኅበረሰባዊ ተጠያቂነት ስትራቴጂ ይፋ መደረጉን ሚኒስትሯ ገልጸዋል። ስትራቴጂው በተለይም የጤና አመራሩ እና ባለሙያው በኅብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመለየት እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።
በጤናው ዘርፍ የመልካም አሥተዳደር ሥርዓት በማሻሻል እና የማኅበረሰብ ተሳትፎን በማሳደግ አገልግሎቱን ማስፋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ተሳታፊዎች በበኩላቸው የማኅበራዊ ተጠያቂነት ስትራቴጅው ዜጎች የጤና አገልግሎት የማግኘት መብታቸውን እንዲጠይቁ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ሚናው የጎላ መኾኑን አንስተዋል።
የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣትም ከኅብረተሰቡ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ “የጤናው ዘርፍ የማኅበራዊ ተጠያቂነት ስትራቴጅ” በሀገር ደረጃ የመጀመሪያ ነው ተብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
