
ባሕር ዳር: ጥር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክር ቤቱ ባካሄደው 16ኛ መደበኛ ሥብሠባው የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አዳምጧል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ አማረች በካሎ (ዶ.ር) የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አስመልክቶ ግብረ መልስ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ የተጣለበትን ታላቅ ሀገራዊ ኀላፊነት በአግባቡ እየተወጣ እና ሪፖርቱም ይህን የሚሳይ ገላጭ እና ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራርን እየተከተለ መኾኑን በጠንካራ አፈጻጸም አስቀምጠዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሴክተሩ የሚታዩ ችግሮችን መለየቱን እና ይህም ችግሮችን ለመፍታት አመቺ በመኾኑ በጠንካራ አፈጻጸም እንደሚወሰድ ገልጸው በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ኢንዱስትሪ በአንድ አካባቢ ብቻ የሚወሰን አይደለም ያሉት ዶክተር አማረች የኢንዱስትሪዎችን አቅም መሠረት ያደረጉ፣ እርስ በእርስ ተያይዘው እና ተመጋግበው የሚሄዱ እና ተወዳዳሪ መኾናቸውን፣ የግብዓት ትስስራቸውን እና አፈጻጸማቸውን ማየት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ መንግሥት የኢንዱስትሪዎችን መገኛ ቦታ ባይወስንም ከፖሊሲ ማበረታቻ ጀምሮ በፍትሐዊነት የሚሠራቸው ሥራዎች ሊኖሩ እንደሚገባም ሠብሣቢዋ ጠቁመዋል፡፡
የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱን ዕቀድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከምክር ቤቱ፣ ከቋሚ ኮሚቴው እና ከምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ተነስተው ሰፊ ውይይት እንደተደረገባቸው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
