
ደሴ: ጥር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተራቆተ መሬትን በማልማት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከአሚኮ ጋር ቆይታ የነበራቸው አርሶ አደሮች ገልጸዋል። ከዚህ በፊት አካባቢያቸው በጎርፍ ይጠቃ እንደነበር የተናገሩት አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም በተሠራ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ለውጥ ማየታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ ቀናትም የተፋሰስ ልማት መሥራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ባለሙያ ሀብታሙ ከበደ በተፋሰስ ከዚህ ቀደም በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እየኾኑ ነው ብለዋል።
በዚህ ዓመት በከተማዋ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ለሚሠራው የተፋሰስ ልማት ሥራ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወን መቆየቱን የገለጹት የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አባይነሽ ፍስሀ ናቸው። የሰው ኀይል ልየታ፣ የልማት መሳሪያዎችን የማዘጋጀት፣ የቀያሽ አርሶ አደሮች ሥልጠና እና ሌሎችም በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ከ5ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት በተፋሰስ ልማት እንደሚሠራ ኀላፊዋ ገልጸዋል። የተፈጥሮ ሀብት ልማት አጀማመር ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉጌታ አቢ ኮምቦልቻ ከተማ የኢንዱስትሪ መንደር እንደመኾኗ የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ለማስጠበቅ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ሠልሀዲን ሰይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
