“የአምራች ኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት አቅም 61 ነጥብ 2 በመቶ ደርሷል” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል

31

ባሕር ዳር: ጥር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ሥብሠባውን እያካሄደ ነው። ምክር ቤቱ በመደበኛ ሥብሠባው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርትን አዳምጧል።

የስድስት ወራት አፈጻጸማቸውን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሀገር ጠቅላላ ምርት ዕድገት፣ ለዘላቂ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለንግድ ሚዛን መጣጣም የማይተካ ድርሻ ያለው የጠንካራ ኢኮኖሚ የማዕዘን ድንጋይ ነው ብለዋል።

ኢንዱስትሪ ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር፣ ለሌሎች ዘርፎች ዕድገት እና መነቃቃት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መኾኑንም አንስተዋል። ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በተያዘው ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ውስጥ ቅድሚያ ከተሰጣቸው አምስት ዘርፎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ አንዱ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ተወዳዳሪ እንድትኾን የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎች እንዳሏትም ተናግረዋል። ያሏትን ምቹ የልማት ዕድሎች በመጠቀምም የዘርፉን ዘላቂ የዕድገት ተስፋ የሚያሳዩ ተግባራት መከናዎናቸውንም ተናግረዋል። የማምረት አቅምን በማሳደግ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የገቢ ምርትን በመተካት፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱትሪዎችን በማሸጋገር፣ ችግር ፈች ምርምር እና ጥናት በማካሄድ የተከናወኑ ተግባራት በጉልህ የሚጠቀሱ መኾናቸውን አንስተዋል። አሁንም መፈታት የሚገባቸው ችግሮች መኖራቸውንም አስታውቀዋል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም ኾነ የሀገር ውስጥ አዳዲስ ባለሃብቶችን ተቀብሎ የማስተናገድ ባሕሉ አልዳበረም ያሉት ሚኒስትሩ ዘርፉ የሚፈልገውን ከፍተኛ የልማት ፋይናንስ ለማቅረብ የባንኮች አቅም ደካማ መኾን፣ የመሠረተ ልማት ተደራሽነት እና ጥራት ከኢንዱስትሪ ባሕሪ ጋር አብሮ ያለመሄድ ጉድለቶች መኖራቸውን ነው የተናገሩት።

የኢንዱስትሪዎችን የኀይል አቅርቦት ለመፍታት 350 ሺህ 600 ኪሎ ዋት ኀይል ለኢንዱስትሪዎች ማቅረብ መቻላቸውንም ገልጸዋል። በጨርቃጨርቅ፣ በምግብ እና መጠጥ፣ በኬሚካል እና ኮንስትራክሽን እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ እና ኢንጂነሪንግ ዘርፎች 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ግብዓት ማቅረባቸውንም ተናግረዋል። ለአምራች ኢንዱስትሪዎች 369 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መቅረቡንም አስታውቀዋል። ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ብድር ማቅረባቸውንም ተናግረዋል።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ማሻሻያው የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እና አቅርቦት እንዲኖር ከፍተኛ እገዛ ማድረጉንም አንስተዋል። የአምራች ኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት አቅም አጠቃቀም 61 ነጥብ 2 በመቶ ማድረስ መቻላቸውንም አስታውቀዋል።

ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ባለፉት ስድስት ወራት የአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ዕድገት እና ትስስር የማሻሻል ሥራ መሥራታቸውንም አመላክተዋል። በበጀት ዓመቱ ምርት ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማገኘቱን እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉንም አስታውቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ ወገኖችን ተደራሽ የሚያደርግ የወባ በሽታ ምርመራ እና ሕክምና ዘመቻ ተጀመረ።
Next articleየኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት አስጀምሯል።