በአማራ ክልል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ ወገኖችን ተደራሽ የሚያደርግ የወባ በሽታ ምርመራ እና ሕክምና ዘመቻ ተጀመረ።

45

ባሕር ዳር: ጥር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት “ትኩሳት ያለባቸውን ሰዎች የወባ ምርመራ እና ሕክምና እንዲያገኙ እንተባበር” በሚል መሪ መልዕክት ለአንድ ወር የሚቆይ ዘመቻ ዛሬ አስጀምሯል። የአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ የምርመራ እና የሕክምና ዘመቻውን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በክልሉ የወባ በሽታ በስፋት ባለባቸው 40 ወረዳዎች ትኩሳት ያለባቸውን ሰዎች ቤት ለቤት በጤና ባለሙያዎች አማካኝነት የመመርመር እና የማከም ዘመቻ ተጀምሯል ነው ያሉት። ዘመቻው እስከ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይም ተናግረዋል። ለመመርመር እና ለሕክምና የሚውል በጀት እና ግብዓት ለተመረጡ ወረዳዎች ተሰራጭቷል ያሉት ዳይሬክተሩ

በቤት ለቤት ምርመራ እና ሕክምና ዘመቻው የወባ በሽታ ለተገኘባቸው ሰዎች ሕክምና ይሰጣልም ነው ያሉት። በክልሉ በጥቅምት ወር አጋማሽ በሳምንት እስከ 82 ሺህ የወባ ሕሙማን ወደ ጤና ተቋማት ይመጡ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ላይ በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ እና ከወቅቱ ጋር ተያይዞ ወባ እየቀነሰ መኾኑንም ገልጸዋል። ባለፈው ሳምንት የተመዘገበው የወባ ሕሙማን ቁጥር 29 ሺህ መኾኑን በአስረጅነት አንስተዋል።

የምርመራ እና ሕክምና ሥራ ለማከናወን የተመረጡት 40 ወረዳዎች አሁንም የክልሉን 70 በመቶ የወባ በሽታ የሚሸፍኑ ናቸው ብለዋል። በእነዚህ ወረዳዎች ውስጥ ትኩሳት ያለባቸው ሰዎችን በሙሉ አግኝቶ መመርመር አስፈልጓል ነው ያሉት በመግለጫቸው። በዘመቻ በተመረጡ ወረዳዎች ያለውን የወባ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ይቻላል ነው ያሉት።

በተለይ በክልሉ ከመጋቢት ወር ጀምሮ መለስተኛ የወባ በሽታ ስርጭት ስለሚኖር ወረርሽኝ እንዳይከሰት ይህ የቤት ለቤት የምርመራ እና ሕክምና ዘመቻ ፋይዳው ከፍተኛ እንደኾነ ነው የተናገሩት። የወባ በሽታን ተሕዋስ ከሰው ደም ውስጥ በማከም እና በማጽዳት ወባ ከበሽተኛው ሰው ወደ ጤነኛው ሰው በትንኟ አማካኝነት እንዳይተላለፍ አስቀድሞ ማከም ይገባል ነው ያሉት። ዘመቻው ውጤታማ እንዲኾን የሁሉንም ቀናዒ ርብርብ እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።

ወባ በቀነሰበት ጊዜ እና ያለወቅቱ አሁን የዘመቻው አስፈላጊነት ለምን አስፈለገ? የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ዘመቻው ወባ ያለባቸውን ሰዎች ለይቶ በማከም ስርጭቱን ለመቀነስ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፤ የመድኃኒትን ብክነትም ቆጣቢ ነው ብለዋል። ዘመቻው ውጤታማ እንዲኾን አጋር ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።ጤና ጣቢያዎች በዋናነት ዘመቻውን እያስተባበሩ እንደሚመሩት እና ሁሉም ሴክተሮች ድጋፍ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

ትኩሳት ያለባቸውን ወገኖች እንዲመረመሩ እና እንዲታከሙ ማድረግ ይገባዋል ነው ያሉት። በተለይም ቤት ለቤት የሚመጡ የጤና ባለሙያዎችን የትኛውም አካል ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል። ለዘመቻው 17 ሚሊዮን ብር በመመደብ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ትኩሳት ያለባቸው ሰዎች የምርመራ እና ሕክምና ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት በመግለጫቸው።

ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክር ቤቱ የተለያዩ ሹመቶችን አጸደቀ ።
Next article“የአምራች ኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት አቅም 61 ነጥብ 2 በመቶ ደርሷል” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል