
ባሕር ዳር: ጥር 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ ዓመት እና የአጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምስረታ ታሪክ ሲነሳ ስማቸው አብሮ ከሚነሱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡
ትናንት በተካሄደው የክብረ በዓሉ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የማካረሪ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ባርናባስ ናዋንዌ ተቋማቸው ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ በትብብር እየሠራ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ አፍሪካ በሁሉም ዘርፍ ዕድገት እያስመዘገበች ያለች አሕጉር ናት ያሉት ፕሮፌሰር ባርናባስ ናዋንዌ እንደ አለመታደል ኾኖ የአሕጉሪቷ ዕድገት እየተመራበት ያለው መንገድ ግን መሠረታዊ ውስንነት እና ክፍተት ያለበት ነው ብለዋል፡፡
ይህንን ክፍተት በመሙላት በኩል ትምህርት በተለይም ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚናቸው ላቅ ያለ መኾን ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የአሕጉሪቷን እድገት በትክክለኛው መንገድ ለመምራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቀራርበው በትብብር መሥራት ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት፡፡
ዩኒቨርሲቲያቸው ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር የጀመረው የጋራ የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ እና እሱን ተከትሎ ያሉ መቀራረቦች ተስፋ ሰጪ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ በባለሙያዎች ድጋፍ፣ በልምድ ልውውጥ እና በተማሪዎች እገዛ እና የምርምር ሥራዎች አብረው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡
በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሏት እና ሀገር በቀል እውቀት የሞላት አፍሪካ ድህነት መለያዋም ኾነ መጠሪያዋ ሊኾን አይገባም ያሉት ፕሬዚዳንቱ “የአፍሪካን ዕድገት በትክክለኛው መንገድ ለመምራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና የጎላ ነው” ብለዋል፡፡
አፍሪካን ከድህነት ነጻ ለማውጣት በጋራ መሥራት እና በትብብር መለወጥ ይጠይቃል፤ ይህንንም ለማድረግ ዝግጁዎች ነን ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
