
አዲስ አበባ: ጥር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የደም እና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለክልል ደም ባንኮች የሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ አድርጓል። መሳሪያዎችንም ለክልል ጤና ቢሮ ኀላፊዎች እና ተወካዮች የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ አስረክበዋል።
12 አይነት መሳሪያዎች ማለትም እንደ ደም ማቆያ፣ መመርመሪያ እና ማጓጓዣ የሚኾኑ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደርገዋል።
በ53ቱ የደም ባንኮች ለጋሾች ደም ሲሰጡ በጥራት እና በብዛት ለተገልጋዮች እንዲደርስ ለደም ባንኮች መሳሪያዎች የሚያስፈልጉ በመኾናቸው ድጋፍ መደረጉን ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ደም ባንክ በኩል በበጎ ፈቃደኝነት ደም በሚለግሱ ወገኖች ብዙ ደም ፈላጊ እናቶችን እና ህጻናትን ሕይወት መታደግ መቻሉን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል። በቀጣይም በጎ ፈቃደኞች ልገሳቸውን በማጠናከር ለሰው ሕይወት መትረፍ መፍትሄ ሊሆኑ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ የደም እና ኅብረ ህዋስ ባንክ ጋር በመተባበር ደም ባንኮች ጥራት ያለው ደም ለተገልጋዮች እንዲያደርሱ እንሠራለን ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
