
ጎንደር: ጥር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምሥረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው። በዓሉ ከጥር 14/2017 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም ድረስ 20 በሚኾኑ ሁነቶች ይከበራል። በዩኒቨርሲቲው የምሥረታ በዓል ላይ ጥሪ የተደረገላቸው የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞን እና የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ዛሬ የተጀመረው እና “የ70 ዓመታት የትምህርት ልህቀት እና የ100 ዓመታት የጤና አገልግሎት” በሚል መሪ መልዕክት የሚከበረው የዩኒቨርሲቲው የምሥረታ በዓል ለሚቀጥሉት አምስት ወራት በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ተብሏል፡፡ በመርሐ ግብሩ መክፈቻ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፋት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው መቋቋሙም ኾነ ማደጉ ከሕዝብ ፍላጎት የመነጨ ነበር ብለዋል። በወቅቱ ደንቢያ እና አካባቢው የተስፋፋው የወባ በሽታ እና እሱን ለመከላከል የሠለጠነ የሰው ኀይል ማስፈለጉ ለዛሬው ትልቅ ሀገራዊ ተቋም መሠረት ኾኗል ነው ያሉት።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር እና የምርምር ሥራዎች ከሀገር በቀል ዕውቀት የተነጠሉ እንደኾኑ ተደጋግሞ ይነሳል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተደራሽነት ያሳየውን ዕድገት ያክል ሀገር በቀል ዕውቀትን ከዘመናዊ ትምህርት ለማዋሐድም ይሠራል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ጥንታዊ ከሚባሉ ሀገሮች መካከል አንዷ ናት ያሉት ፕሬዚዳንቱ “ከተቋም ግንባታ፣ ከተቋም አመራር እና ከተቋማት ቀጣይነት አኳያም ያለን ባሕል በሚገባ ሊፈተሽ ይገባል” ብለዋል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ተቋቁሞ ለጎንደር አካባቢ ብቻ ሳይኾን ለመላው ኢትዮጵያ እና ለሌሎችም የአፍሪካ መገኖች ምሥጉን ምሩቃንን በማፍራት፣ በምርምር፣ በሕክምና እና በማኅበረሰባዊ አገልግሎት ሰፊ ሥራ ሢሠራ ቆይቷል ብለዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሰባት አስርት ዓመታትም ኾነ አንድ ምዕተ ዓመት መልካም ስም ያለው ተቋም ይዞ ዛሬ ላይ ለመድረስ ብዙ አጋሮቹ ሚናቸው የላቀ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ በታሪክ አጋጣሚ ዛሬ ከፊታችሁ ቆመን ስለአበርክቷችሁ እናመሠግናለን ማለት እፈልጋለሁ ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
