በተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ለማሳ እርከን ሥራ ሰፊ ትኩረት ይሰጣል።

22

ደባርቅ: ጥር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የ2017 ዓ.ም የተፈጥሮ ሀብት ልማት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናውኗል። መርሐ ግብሩ በከተማ አሥተዳደሩ ስር በሚገኙ አምስት የገጠር ቀበሌዎች በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ተጀምሯል።
የተፈጥሮ ሃብት ልማት የአካባቢን ሥነ-ምህዳር ከማስጠበቅ አኳያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተደጋግሞ ይነሳል።

የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ልዑል መስፍ የተረጋጋ የአረንጓዴ ምጣኔ ሀብትን ለማሳደግ እና ማኅበረሰባዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተፈጥሮ ሀብት ልማት አይነተኛ መፍትሔ እንደኾነ ገልጸዋል። የተፈጥሮ ሀብት ልማት አርሶ አደሩ ከተፈጥሮ ጋር ያለው መስተጋብር ጤናማ እንዲኾን እና አንዱ ያንዱን ህልውና እንዲያረጋግጥ ያግዛል ነው ያሉት።

የከተማ አሥተዳደሩ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በዕውቀት አየነው በዘንድሮው ዓመት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ ለማሳ እርከን ሥራ ትኩረት አንደሚሠጥ ነው ያስገነዘቡት። ዕቅዱንም ለማሳካት ከ4 ሺህ በላይ የሰው ኀይል እና ከ3 ሺህ በላይ የልማት መሳሪያ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ልማት የአፈር መሸርሸርን እና ሌሎች መሰል ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል አስፈላጊ በመኾኑ የጋራ መግባባት ተወስዶ እየተሠራ እንደኾነ የአካባቢው አርሶ አደሮች ተናግረዋል። አቶ መሃባው ተሳሃለኒ የተባሉ የደብር ቀበሌ ነዋሪ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥቅምን መረዳት በመቻላቸው ከምንጊዜውም በላይ በተነሳሽነት እየሠሩ እንደኾነም ጠቁመዋል።

የደብር ቀበሌ ዋና አሥተዳዳሪ ቄስ ግርማይ ተረፈ አርሶ አደሩ ኑሮውን ለማሻሻል እና የሚጋረጥበትን ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ፈተና ለማለፍ ተፈጥሮን መንከባከብ ምርጫው አድርጎ እየሠራ ነው ብለዋል። የተፈጥሮ ሀብት ልማት ወቅታዊ የዘመቻ ሥራ ሳይኾን ቀጣይነት ያለው እና አሳታፊ ሊኾን እንደሚገባም ተጠቅሷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአንደኛው ዙር የመስኖ ልማት ከ32 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
Next article“የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተደራሽነት ያሳየውን ዕድገት ያክል ሀገር በቀል ዕውቀትን ከዘመናዊ ትምህርት ለማዋሐድም ይሠራል” አስራት አጸደወይን (ዶ.ር)