ብልጽግና ፓርቲ ለመተግበር ቃል የገባቸው ጉዳዮች በአግባቡ እየተተገበሩ መኾናቸውን አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

33

ባሕር ዳር: ጥር 14/2017 ዓ.ም(አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የሩዋንዳ አምባሳደር ቻርለስ ካራምባ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸው በሁለቱ ሀገራት መንግሥታዊ እና ፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል። የፓርቲ ለፓርቲ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙትን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ውይይቶችንም አድርገዋል።

ኢትዮጵያ የኮሪደር ልማት ፣አረንጓዴ አሻራ ፣በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና በምግብ ዋስትና ራስን ለመቻል የጀመረቻቸው ሥራዎች አበረታች መኾናቸውም በውይይቱ ተነስቷል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ብልጽግና ፓርቲ በአንደኛው መደበኛ ጉባኤ ለመተግበር ቃል የገባቸው ጉዳዮች በአግባቡ እየተተገበሩ መኾናቸውን አንስተዋል። በዚህም በየዘርፉ ስኬቶች እየተመዘገቡ መኾኑን ገልጸዋል። በሁለተኛው የፓርቲው መደበኛ ጉባኤ የተገኙ ስኬቶችን የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች እንደሚጠበቁም አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች፣ ቀጣይ ግቦች እና ራዕዮች ላይም ገለጻ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የሩዋንዳ አምባሳደር ቻርለሰስ ካራምባ በፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ እንድንሳተፍ በመጋበዛችን እናመሰግናለን ብለዋል።

ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ከሩዋንዳው ገዢ ፓርቲ ረፒፍ (RPF) በጉባኤው ላይ የሚሳተፍ የልዑክ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል ተብሏል። የሀገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክሩ የሁለትዮሽ ውይይቶች እንደሚደረጉም አንስተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ወሎ ዞን በዓይና ቡግና ወረዳ ለተቸገሩ ወገኖች የዕለት የምግብ ድጋፍ ተደረገ።
Next articleከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት በትምህርት ላይ የተፈጠረውን ችግር እንደሚፈታ የትምህርት ቢሮ ገለጸ።