
ባሕር ዳር: ጥር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “የዜጎች ተሳትፎ ለተሳካ አካታች ሀገራዊ ምክክር እና ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት በርካታ አካላት የተሳተፉበት ፎረም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተካሄደ ነው። በፎረሙ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ.ር) የሀገራዊ መግባባት ግንባታ በርካታ ውጣ ውረዶች ያሉት እና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ መኾኑን ገልጸዋል።
የሀገራዊ መግባባት አለመኖር የእርስ በእርስ ግጭቶችን በመፍጠር ለኢኮኖሚያዊ ድቀት እና ለውጭ ጠላት ሴራ ተጋላጭ እንደሚያደርግም አመላክተዋል።
ከታሪክ ስህተት እና ጥፋት ለመማር ዝግጁ መኾን፣ ለትውልድ የሚሻገሩ ጉዳዮች ሌሎች ችግሮችን ሳይወልዱ መፍትሔ መስጠት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚወሰድ ትምህርት ነው ብለዋል። ሀገራዊ አንድነት መገንባት የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሥርዓት ለመፍጠር እና ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማዳበር ያስችላል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ያገኘችውን ሀገራዊ ምክክር የማድረግ ዕድል ሁሉም አካላት በአግባቡ መጠቀም እና እንዳይበላሽ በቁርጠኝነት መጠበቅ እንደሚገባቸው ማሳሰባቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
