ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት አሁንም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለጸ።

67

ባሕር ዳር: ጥር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2017 የትምህርት ዘመን የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።

በግምገማው ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ የሚገኙ የትምህርት መሪዎች፣ የዞን አሥተዳዳሪዎች፣ ከንቲባዎች፣ የብልጽግና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች፣ የመምህራን ማኅበር መሪዎች ፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ርዕሰ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እና የኅብረተሰብ ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

በግምገማው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ የክልሉ ትምህርት በርካታ ፈተናዎች እንደገጠሙት ገልጸዋል። ይህንኑ ፈተና ማለፍ በሚቻልባቸው መፍትሔዎች ላይ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በ2016 የትምህርት ዘመን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ከትምህርት ውጪ ኾነው መክረማቸውንም አስታውሰዋል። በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ይህንን ለማካካስ በድምሩ 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስመዝገብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም አንስተዋል። ይሁንና አሁንም በሰላም እጦቱ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች መማር እንዳልቻሉ ገልጸዋል። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ትምህርት ቤት ለመጡ ተማሪዎች የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተፈታኞችን ለማብቃት እና ቀሪ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።

የትምህርት ቤቶችን ግብዓት በማሟላት እና የወደሙትን በመጠገን መሥራት ሌላኛው ሥራ መኾኑን ጠቅሰዋል። ለዚህም የኅብረተሰቡ ተሳትፎ አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን በክልሉ መንግሥት በጀት እንዲደገፉ ለማድረግ እየተሠራ ነው።
Next articleየትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የጎንደር አብያተ መንግሥታት እድሳትን ጎበኙ።