
ወልድያ: ጥር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢዎች እና አባላት በወልድያ ከተማ አሥተዳደር የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ምልከታ፣ ቁጥጥር እና ድጋፍ አድርገዋል። ከሌማት ትሩፋት አኳያ ለተደራጁ ወጣቶች ሥራ የተፈጠረባቸው የንብ ሀብት እና የዶሮ እርባታ ማዕከላት፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ የሚያቀርብ የዳቦ መጋገሪያ እና ለዝቅተኛ ነዋሪ ወገኖች ተሠርተው የተላለፉ ቤቶች ተጎብኝተዋል።
በተጨማሪም ፖሊስ፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት እና በከተማ አሥተዳደሩ የውስጥ ገቢ የሚሠራው የ30 ሜትር የቀለበት መንገድ የጉብኝቱ አካል ነበሩ። የበጀት እና ፋይናስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ሀናን አብዱ የሥራ ዕድል ፈጠራው ቋሚ መኾኑ እና ከሌማት ትሩፋት ጋር ተቀናጅቶ ወጣቶች እና የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርግ መኾኑ አበረታች ነው ብለዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ከማኅበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊ እና ከመልካም አሥተዳደር አኳያ በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖ የሠራው ተግባር አርዓያነት ያለው ስለመኾኑም ነው ያብራሩት። በአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የውኃ ሀብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮምቴ ሠብሣቢ ከፍያለው ሙላቴ ከተማ አሥተዳደሩ የሚሠራቸው የቀለበት መንገድ፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች የበጀት እጥረት እንዳለባቸው ስለመመልከታቸው ነው ያስገነዘቡት።
ልማቶቹ ጉልህ የኾኑ እና ሕዝብን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በመኾናቸው በክልሉ መንግሥት የበጀት ድጋፍ እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው የክልል ቢሮዎች እና ከክልሉ መንግሥት ጋር ምክክር ይደረጋል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
