
ባሕር ዳር: ጥር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ ጥቅም እና በሕዝብ ተጠቃሚነት ላይ የጋራ መግባባትን ማጠናከር እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል። በብሔራዊ መግባባት ላይ ያተኮረው ሁለተኛው የፓርላማ የዜጎች መድረክ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መካሄድ ጀምሯል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በመክፈቻ ንግግራቸው ብሔራዊ መግባባት ለሀገር ሰላም እና ብልጽግና ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። የዛሬው መድረክ ዓላማም በብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነት እና ተግዳሮቶች ላይ በጋራ ለመምከር ነው ብለዋል። ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ የአመለካከት ልዩነቶች ጤናማ እና ሕገ መንግሥታዊ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል።
ይሁንና በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ በብሔራዊ ጥቅም እና በሕዝብ ተጠቃሚነት ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት እና የጋራ አቋምን ማጠናከር ይገባል ብለዋል። “ቀደምት ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው ኢትዮጵያን ከወረራ ጠብቀው እና አስከብረው ሀገር ማስቀጠላቸውንም” አስታውሰዋል።
የዛሬው ትውልድ በውስብስቡ የዓለም ኹኔታ በመቻቻል፣ በአንድነት፣ በበጎነት፣ በሕገ መንግሥታዊ እና በሕግ የበላይነት መርሕ የሀገርን ዘላቂነት እና ሉዓላዊ ጥቅምን ማረጋገጥ የግድ መኾኑንም ጠቅሰዋል። በማንስማማባቸው ጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያለ ምክክር በማድረግ ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል ያሉት አፈ ጉባኤው ለዚህም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
እስካሁንም በ10 ክልሎች እና በሁለት ከተማ አሥተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተሳታፊ ልየታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልጸዋል። ኢትዮጵያውያን ለምክክሩ ስኬት እና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በንቃት እና በብስለት እንዲሳተፉ መጠየቃቸውንም ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
