
ጎንደር: ጥር 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ ዓመት ምስረታ እና 100ኛ ዓመት የጎንደር ሆስፒታል ምስረታ በዓል ከጥር 14/2017 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡ “የ70 ዓመታት የትምህርት ልህቀት እና የ100 ዓመታት የጤና አገልግሎት” በሚል መሪ መልዕክት የሚከበረው የምስረታ በዓል ለሚቀጥሉት አምስት ወራት በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ተብሏል፡፡
የምስረታ በዓሉን አከባበር አስመልክቶ በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር) የበዓሉ መከበር ዓላማ ዩኒቨርሲቲው በትናንት፣ ዛሬ እና ነገ መካከል የተንሰላሰለ ሂደት እንዲኖረው ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ትውልድ በማነጽ እና የሕክምና አገልግሎት በመስጠት 100 ዓመታትን ለተጓዘው የምስረታ በዓሉ ታሪኩን እና አበርክቶውን የሚመጥን እንዲኾን በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አብራርተዋል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በስፋት ከሚታዎቅባቸው ሥራዎቹ መካከል አንዱ የማኅበረሰብ አገልግሎት መሥጠት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ተቋሙ በተማሪዎቹ እና በአካባቢው ማኅበረሰብ መካከል ጥብቅ ቁርኝት እንዲፈጠር መሥራት ችሏል ብለዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሀገርን የፈተኗት ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ መሰናክሎችን ተቋቁመው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራዎች ለማከናወን ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
2012 ዓ.ም የተጀመረው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቃልኪዳን የቤተሰብ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ አራቱም አቅጣጫዎች የሚመጡ ተማሪዎች ባይተዋር ሳይኾኑ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ተቋማዊ መልክ ይዟል ያሉት ፕሬዚዳንቱ “የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቃልኪዳን የቤተሰብ ፕሮጀክት ከጎንደር ሕዝብ ሀገር በቀል እሴት የተቀዳ ነው” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የተጋረጠባቸውን አንድነት የሚሸረሽሩ ፈተናዎችን ለመሻገር የሚያስችሉ ስልቶችን እና አሠራሮችን መቀየስ ያስፈልግ ነበር ነው ያሉት። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቃል ኪዳን የቤተሰብ ፕሮጀክት ይህንን ፈተና በማለፍ በርካታ መንገዶችን እንደተጓዘ አስገንዝበዋል፡፡ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ብቸኝነት እንዳይሰማቸው ከማኅበረሰቡ ጋር ከማቀራረብ ባለፈ የተማሪዎቹ ቤተሰቦች አንዲተዋወቁ እስከ ማድረግም ተሸጋግሯል ነው ያሉት፡፡
ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ትክክለኛ ገጽታ እና እውነተኛ ማንነት ለሌሎች በማስተዋወቅ በኩል አይነተኛ ሚና እንዳለው አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም በስፋት፣ በጥልቀት እና በልዩ ክትትል ከሚሠራባቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ምስረታ በዓል መርሐ ግብር ከተያዘላቸው ሁነቶች መካከል አንዱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቃል ኪዳን የቤተሰብ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ስኬቶች፣ ፈተናዎች እና የተገኙ ውጤቶች ቀርበው ለሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሞክሮ ይኾናሉ ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
