ከ500 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የወባ በሽታ ምርመራ እና የሕክምና ንቅናቄ ሊካሄድ ነው።

41

ባሕር ዳር: ጥር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ትኩሳት ያለባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመቻ የወባ በሽታ ምርመራ እና ሕክምና መስጠት የሚያስችል ንቅናቄ ሊያደርግ ነው። የንቅናቄ ዘመቻው ከጥር 15 እስከ የካቲት 15/2017ዓ.ም የሚቆይ መኾኑም ተመላክቷል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በክልሉ ባላፈው አንድ ሳምንት ብቻ እስከ 29 ሺህ የወባ ሕሙማን በጤና ተቋማት ታክመዋል ብለዋል። ካሁን ቀደም የወባ በሽታን ሪፖርት አድርገው የማያውቁ ቀበሌዎች አሁን ላይ ሪፖርት ማድረግ መጀመራቸው የስርጭቱን ስፋት ያሳያል ያሉት ዳይሬክተሩ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በንቅናቄ ዘመቻ መሥራት አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷል ነው ያሉት።

በዘመቻው የጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት በመዘዋወር የወባ በሽታ ምልክት ያለባቸውን ሰዎች በፈጣን መሣሪያ በመመርመር ያክማሉ ብለዋል። በምርመራው ጤና ጣቢያዎች በስፋት ተሳታፊ ይኾናሉ ነው ያሉት። ወባ የኅብረተሰቡ ችግር እንዳይኾን በዘመቻው ሁሉም በትብብር መሥራት ይጠበቅበታል ያሉት ዳይሬክተሩ የመድኃኒት እና የገንዘብ አቅርቦት ወደ ወረዳዎች ደርሷል ብለዋል።

በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የወባ ተህዋስያን አስቀድሞ ማከም ከተቻለ ትንኟ ምልክቱ ካለበት ሰው ደም ወደ ጤነኛው ሰው ማስተላለፍ እንዳትችል በማድረግ የወባ በሽታ ስርጭትን በከፍተኛ ኹኔታ መቀነስ ይቻላል ነው ያሉት። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ መልካሙ ጌትነት ክልሉ ባጋጠመው የጸጥታ ችግር የተነሳ የጤና ባለሙያዎች ተንቀሳቅሰው ማከም ባለመቻላቸው የወባ በሽታ ሥርጭት ከፍ ብሏል ነው ያሉት። በተለይም ሕጻናትን እና እናቶችን ተጠቂ አድርጓቸዋል ብለዋል። የወባ በሽታን ምንጭ የኾነውን ሰው አስቀድሞ በማከም የበሽታውን ስርጭት መግታት ይገባል ነው ያሉት።

በክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ አማካሪ ይርዳው እምሩ ከ2010 ዓ.ም በኋላ የወባ በሽታ በየዓመቱ የሕሙማን ምጣኔ እየጨመረ መኾኑን ገልጸዋል።

በ2017 ግማሽ ዓመት ብቻ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ሕሙማን ተመዝግበዋል ነው ያሉት። ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ቁጥር ጨምሯል ነው ያሉት። ስርጭቱ በስፋት የሚስተዋልባቸውን 40 ወረዳዎች በመምረጥም በዘመቻ ሕሙማንን ለይቶ የማከም ሥራ ይከናዎናል ብለዋል።

ለዘመቻውም 17 ሚሊዮን ብር በመመደብ ከ505 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሠራል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአየር ኃይል ለመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ።
Next articleበደሴ ዙሪያ ወረዳ በ62 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የመስኖ ፕሮጀክት ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።