
ጎንደር: ጥር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርስቲ የምሥረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብራል። የጎንደር ዩኒቨርስቲ 70ኛ ዓመት እና አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 100ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል። የበዓል አከባበሩን አስመልክቶ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር) ለብዙኀን መገናኛ ተቋማት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ከመጀመሪያው ትውልድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ የኾነው እና አንጋፋው ጎንደር የኒቨርሲቲ አንድ ምዕተ ዓመት ካስቆጠሩ የሀገሪቷ ውስን ተቋማት መካከል አንዱ ነው። ዩኒቨርሲቲው ከምስረታው ጀምሮ ለሀገሪቷ ዘርፈ ብዙ ለውጥ ድርሻው የጎላ ነው። ከሕክምና እስከ ግብርና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብዙ እና ጉልህ አበርክቶዎች አሉት።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምስረታ ከሕዝብ ፍላጎት የመነጨ ነበር ያሉት የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር) በጎንደር እና አካባቢው የነበረውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመግታት ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደተመሠረተ ተናግረዋል። ከተመሠረተበት ወቅት ጀምሮም ደረጃ በደረጃ እራሱን እያሳደገ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ መድረሱን አንስተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ጊዜ ከ12 በላይ የምርምር ተቋማት እና 22 ግቢዎች እንዳሉት ዶክተር አስራት ጠቁመዋል። የጣሊያን ኮንስሌት ለቸቸላ ሆስፒታል መመሥረትም ምክንያት እንደኾነ ጠቁመዋል። የበዓሉ መከበር በርካታ ዓላማዎች አሉት ያሉት ፕሬዚዳንቱ “ዋናው ዓላማም ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን የሚያስተሳስር ማድረግ ነው” ብለዋል።
የትናንቶችን መዘከር እና ማመስገን፤ ዛሬ ተቋሙ ያሉበትን ደረጃ ማየት እና ከነገ ጋር ማንሰላሰል መኾኑን አንስተዋል። በዓሉ ወደ 20 የሚጠጉ መርሐ ግብሮች አሉት ያሉት ፕሬዚዳንቱ ስፖርታዊ ውድድር፣ ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት፣ የቃል ኪዳን ቤተሰብ መርሐ ግብር፣ የተማሪዎች ምረቃ መርሐ ግብር፣ የታወቂ ሰዎች ተሞክሮ ማስፋፊያ መድረክ፣ የፕሮጀክት ሥራዎች ምረቃ፣ የአውደ ርዕይ መርሐ ግብር፣ የተማሪዎች ሳምንት መርሐ ግብር፣ ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ፣ አስተዋፅኦ ያላቸው ቤተሰቦች የሕንጻ ስያሜ፣ አንረሳችሁም የሚል የምስጋና መርሐ ግብር፣ የአካባቢ ቀን መርሐ ግብር፣ የ100 ዓመት ጉዞ መጽሐፍ ምረቃ መርሐ ግብር፣ የምሩቃን ቀን፣ የመሠረተ ልማት ማስጀመር መርሐ ግብር፣ ለዩኒቨርሲቲው ርስታቸውን የለቀቁ አርሶ አደሮችን ለመዘከር የገበሬዎች ቀን እንደ አንድ መርሐ ግብር ተይዟል ብለዋል።
በተጨማሪም የፕሬዚዳንቶች ወግ የሚል መርሐ ግብር፣ የጎንደር ቀን መርሐ ግብር እና በመጨረሻም የምስጋና ቀን ከጥር 17/2017 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም ይከበራል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
