
ባሕር ዳር: ጥር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ባለሃብቶች እና የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚያሠራቸውን የልማት እና ከተማዋን የማዘመን ሥራዎችን ተመልክተዋል። የንግዱ ማኅበረሰብ እና ባለሃብቶች ከተመለከቷቸው ሥራዎች ውስጥ የባሕር ዳርን ሰላም የሚጠብቀው ዘመናዊ የሲሲቲቪ ካሜራ ይገኝበታል። ካሜራው በቅርቡ ተገጥሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።
ቴክኖሎጂውን ያስጎበኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ሲሲቲቪ ካሜራው እና የተገጠመለት አጠቃላይ አሠራር የከተማዋን እና የነዋሪዎቿን ሰላም ለመጠበቅ የሚያስችል ነው ብለዋል። አሠራሩ በከተማዋ ሁሉም አካባቢዎች ያለውን እንቅስቃሴ በአንድ ቦታ ተቀምጦ ለመቆጣጠር የሚያስችል መኾኑን አብራርተዋል። ቴክኖሎጂው በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ታግዞ የሚሠራ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው
የጸጥታ ስጋት ይፈጥራል ተብሎ የተጠረጠረን እንቅስቃሴ ለይቶ በማውጣት እና የግለሰቡን ማንነት በመለየት አጋልጦ ለሕግ እንደሚሰጥም ተናግረዋል። ከተማ አሥተዳደሩ ይህንን እና መሰል ለሕዝብ ሰላም እና ልማት የሚያገለግሉ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። ከከተማዋ ተጠቃሚ ለመኾን የሚፈልግ ማንኛውም አካል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በሚችለው ሁሉ መደገፍ አለበት ነው ያሉት።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ ባለሃብቶም እየተሠሩ ያሉ ልማቶችን አድንቀዋል። የልማት ሥራዎች የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በጽናት በማለፍ የሚከናወኑ መኾናቸው የተናገሩት ባለሀብቶቹ መሪዎችን አመስግነዋል።በጋራ በመቆም የባሕር ዳርን ሰላም መጠበቅ፣ ልማቷንም ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
ተፈጥሮ በነበረው የሰላም እጦት ችግር ከተማዋን ዋጋ እንዳስከፈላት፣ የነዋሪዎችን ኑሮም እንደፈተነ አንስተዋል። ባሕር ዳር አሁን ወደሰላሟ መመለሷንም ጠቅሰዋል።
ባሕር ዳር ሰላሟ የተጠበቀ፣ በልማት የዘመነች እና ለነዋሪዎቿ የምትመች እንድትኾን መንግሥት እየሠራ መኾኑን መመልከታቸውን የገለጹት ጎብኝዎች እነሱም ለከተማቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
