“ቤተ ክርስቲያን የዓለማዊውም ኾነ የመንፈሳዊ ዕውቀት ምንጭ ናት” ብጹዕ አቡነ አብርሃም

44

ባሕር ዳር: ጥር 13/2017 ዓ.ም(አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ በተለምዶ ዓባይ ማዶ ሰፈነ ሰላም ቅድስት አርሴማ እየተባለ ከሚጠራ ቦታ ላይ የአራቱ ጉባኤያት ኮሌጅ እና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ለማቋቋም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል። የመሠረት ድንጋዩን ያስቀመጡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሃም ናቸው።

በዕለቱ ንግግር ያደረጉት ብጹዕ አቡነ አብርሃም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረቶቿ የአብነት ትምህርት ቤቶች ናቸው ብለዋል። “ቤተ ክርስቲያን የዓለማዊውም ኾነ የመንፈሳዊ ዕውቀት ምንጭ እንደኾነች” ገልጸዋል። በዘመናዊውም ኾነ በመንፈሳዊ ዕውቀቱ የበሰለ ትውልድን ለማፍራት የእነዚህ አይነት ተቋማት ሚና ከፍተኛ እንደኾነ ተናግረዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች እንቅፋቶች ገጥመውት የነበረው ይህ ኮሌጅ ሕጋዊ አሠራርን መሠረት አድረጎ መጓዝ በመቻሉ ፍሬ ማፍራት እንዲጀምር አስችሎታልም ነው ያሉት። ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ሁሉ ውብ ተፈጥሮ እና ልምላሜ አለ ያሉት ብጹዕነታቸው በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድን ማፍራት ዓብይ ተግባር መኾኑን አንስተዋል።

የቤተ ክርስቲያን መገለጫዋ አንድነት፣ሰላም፣ ፍቅር እና ችግርን ተጋግዞ ማለፍ ናቸውም” ብለዋል። በመተጋገዝ እና አብሮ በመቆም እንደነዚህ አይነት ለበጎ ዓላማ የቆሙ ተግባራትንም ማከናወን ይቻላል ነው ያሉት። የመሠረት ድንጋዩ ዛሬ ይቀመጥ እንጅ ቀድመው ወደ ተግባር የገቡ ተግባራት እንዳሉም ብጹዕነታቸው ጠቁመዋል። ለአብነትም የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን ማስተማር መጀመሩን አንስተዋል።

ሊቀ ጠበብት ስጦታው አያሌው በባሕር ዳር ከተማ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ናቸው። ዛሬ መሠረተ ድንጋዩ የተቀመጠው የቤተ ጉባኤ ኮሌጅ እና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ለሀገርም ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል። ተግባሩ የማኅበረሰብ መሠረትም ሊኾን የሚችል እንደኾነ ገልጸዋል።

የመጽሐፍት ትርጓሜ መምህሩ ኃይለ ማርያም ዘውዱ እንዲህ አይነት ኮሌጆች እውነተኛ ሰዋዊ ባሕሪን የተላበሱ ዜጎችን ለማፍራት ምንጭ ኾኖ የሚያገለግል ነው ይላሉ። የተማረ ትውልድ ብዙ በጎ ነገር ይሠራልና ሊደገፍ የሚገባው ተግባር ስለመኾኑም ገልጸዋል። የሕግ ምንጭ የኾነችውን ቤተ ክርስቲያንን ለትውልዱ ለማስተላለፍም ሚናው ከፍተኛ ነውም ብለዋል።

የመሠረተ ድንጋይ የተቀመጠለት የቤተ ጉባኤ ኮሌጅ እና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በቤተ ክርስቲያኗ እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ የሚተገበር ነው ተብሏል። በመንፈሳዊው በኩል አራቱ ጉባኤያት የሚማሩበት ሲኾን በዘመናዊው ትምህርት ቤት ደግሞ በቀጣይ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ለማስተማር ዕቅድ ያለው ተቋም እንደኾነም ተገልጿል።

ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ በልዩ ትኩረት ይሠራል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next articleለከተማዋ ሰላም እና ልማት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የባሕርዳር ከተማ ባለሀብቶች እና ነጋዴዎች ተናገሩ።