”የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ በልዩ ትኩረት ይሠራል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

78

ባሕር ዳር: ጥር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በምዕራብ አማራ ቀጣና የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ የማኅበረሰብ ተፋሰስ ልማት የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል። ”የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ለዘላቂ ምርታማነት ዕድገት” በሚል መሪ መልዕክት በተደረገው የንቅናቄ መድረክ የግብርና ቢሮ እና የተጠሪ ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በዓመቱ የሚሠራው የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ ባለፉት ዓመታት ከነበሩት በተለየ መንገድ በልዩ ትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ልማቱ ሥራ ኅብረተሰቡን ማስተባበር እንደሚጠይቅ እና ሰላም እንደሚፈልግም ገልጸዋል። የሰሜኑ ጦርነት እና በክልሉ የተፈጠረው የእርስ በእርስ ግጭት ደግሞ በሥራው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

በተለይ ባለፈው ዓመት የታቀደው ሥራ በግጭቱ ምክንያት አነስተኛ አፈጻጸም ነበረው ነው ያሉት። የፌዴራል እና የክልሉ የጸጥታ ተቋማት ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅተው ባደረጉት ርብርብ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ የግብርና ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ገልጸዋል።

መላው የገጠሩን ማኅበረሰብ በማንቀሳቀስ እና በማደራጀት ሕይወቱን የሚቀይር የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ እንዲሠራ ማድረግ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል። በተቀመጡ ግቦች እና ፋይዳቸው ላይ ግልጽነት መያዝ ሥራውን በፍጥነት እና በጥራት ለመፈጸም ያስችላል ነው ያሉት።

የንቅናቄ መድረኩም ባለፉት ዓመታት የተሠሩት ሥራዎች፣ የተመዘገቡ ውጤቶች እና ያጋጠሙ ፈተናዎችን በማየት ለሌላ የላቀ ሥራ ውይይት የሚደረግበት መኾኑን ድረስ ገልጸዋል። ለውጤታማነቱም ሕዝቡን አነቃንቆ ወደ ልማቱ በማውጣት ችግሮችን በመፍታት በኩል የተቀመጡ ግቦችን ማሳካት ይጠበቃልም ብለዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ የክልሉ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት እንዲገባ የሚደረግበት፣ የተጀመረውን የግብርና ሽግግር በማረጋገጥ ለምርት እና ምርታማነት ዕድገት ጉልህ ሚና እንዲጫዎት የሚደረግበት እንደኾነም ገልጸዋል።

እጅ ለእጅ ተያይዞ በመሥራት ታሪካዊ ኀላፊነትን መወጣት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article” ኢትዮጵያ ጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሠራች ነው” በለጠ ሞላ (ዶ.ር)
Next article“ቤተ ክርስቲያን የዓለማዊውም ኾነ የመንፈሳዊ ዕውቀት ምንጭ ናት” ብጹዕ አቡነ አብርሃም