” ኢትዮጵያ ጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሠራች ነው” በለጠ ሞላ (ዶ.ር)

56

ባሕር ዳር: ጥር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢጋድ ሀገራት ውስጥ የኢንተርኔት መሠረተ ልማትና የቁጥጥር ማዕቀፎችን ለማጠናከር የሚያስችል የ2025 የኢንተርኔት ልማት ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ኮንፈረንሱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከበይነመረብ ማኅበረሰብ እና ከዊንጉ አፍሪካ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው ። በአፍሪካ ኢጋድ ሀገራት የኢንተርኔት ስነ ምህዳር መሠረት ለመጣል የሚያስችል የኢንተርኔት ልማት ኮንፈረንስ መኾኑም ተመላክቷል። የኢንተርኔት ልማት ኮንፈረንስ (አይዲሲ) 2025 በአፍሪካ ኢጋድ ሀገራት ውስጥ የኢንተርኔት መሠረተ ልማትና የቁጥጥር ማዕቀፎችን ለማጠናከር ያለመም ነው ተብሏል።

በኮንፈረንሱ መልዕክት ያስተላለፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ሁሉንም ዜጎች የሚያጎለብት፣ በአፍሪካ ዲጂታል አብዮት ግንባር ቀደም እንድትኾን የሚያስችል፣ ጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሠራች ነው ብለዋል።

ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ እና በሰፊው የኢጋድ ቀጣና ያለውን ዲጂታል መልክዓ ምድር ማሳያ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂያችን በመመራት የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አስደናቂ እድገት እያስመዘገበ መኾኑን ገልጸዋል። የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጉዞ የወደፊት ሕይወታችን ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ፍትሐዊ መኾኑን ለማረጋገጥ ለሳይበር ደኅንነት ፣ ለዳታ ጥበቃ እና ለዲጂታል እውቀት ቅድሚያ መሰጠት አለበት ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የቴሌኮም መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድ አመርቂ ምዕራፎችን መከናዎናቸውንም ገልጸዋል። የአራተኛው ትወልድ የኢንተርኔት አገልግሎት (የ4ጂ) ሽፋኑን ወደ 34 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን የተናገሩት ሚኒስትሩ የአምስተኛው ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎት (5ጂ) በ14 ከተሞች መጀመሩ ተናግረዋል።

የሞባይ ደንበኞች ቁጥር 80 ነጥብ 5 ሚሊዮን መድረሱንም ገልጸዋል። የሞባይል ብሮድባንድ ተጠቃሚዎች ቁጥር 45 ሚሊዮን ማለፉ በሀገር ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የመጡ ለውጦች ማሳያዎች ናቸው ብለዋል። ከዲጂታል መተግበሪያዎች አንጻር ቴሌቢር ከ51 ነጥብ 54 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን ማፍራቱንም ገልጸዋል።

በዝግጅቱ ላይ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ የኢንተርኔት ልማት ኮንፈረንስ ጠንካራ እና ይበልጥ የተቀናጀ የኢንተርኔት ስነ ምህዳር መሠረት ይጥላል ብለዋል። ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ አጋር አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጅቡቲ ወደብ የደረሰው የአፈር ማዳበሪያ ወደ ኢትዮጵያ እየተጓጓዘ መኾኑ ተገለጸ።
Next article”የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ በልዩ ትኩረት ይሠራል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)