
ደሴ: ጥር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ዞናዊ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ ተካሂዷል። በተፋሰስ ሥራ አጀማመሩ ላይ የአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ኀላፊ ዳኝነት ፋንታ (ዶ.ር)፣ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ ዳኛው፣ የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም እንዲኺም የዞን እና የወረዳ መሪዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የደሴ ዙሪያ አርሶ አደሮች ቻሌ የሱፍ እና ሼህ እብሬ አያሌው የተፋሰስ ልማት ሥራን በመተግበራቸው በየዓመቱ ተጨባጭ ውጤት ማየት መጀመራቸውን ጠቁመዋል። ተፋሰሱ ከእንሰሳት ንክኪ ነፃ እንዲኾኑ የማድረግ ሥራዎችን እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የደሴ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌታቸው እርጋታው ሥራውን ለማከናወን የሚያስችል በቂ የሰው ኃይል እና ግብዓት መዘጋጀቱን ተናግረዋል። ተግባሩንም በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በትኩረት እንሠራለን ነው ያሉት።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጋሎ ለዘርፉ ባለሙያዎች በወረዳ እና በቀበሌ ተገቢው ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። በዞኑ በ520 ቀበሌዎች 1 ሺህ 446 ተፋሰሶች ላይ ከ85 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን ለማልማት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተው ወደ ተግባር ተገብቷልም ነው ያሉት።
ለ30 ቀናት በሚቆየው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በዞኑ ከ600 ሺህ በላይ የሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል። በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ ዳኛው ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ለሥራ እድል ፈጠራ እና የአካባቢን ሥነ ምኅዳር ለመቀየር ዘላቂነት ያለው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም የሚሠሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ዘላቂ ጥቅም እንዲሠጡ ሁሉም ኅብረተሠብ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት አለበት ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
