
ጎንደር: ጥር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” የኤግዚቢሽን እና ውይይት መድረክ በጎንደር ተጀምሯል። በኤግዚቢሽን እና የውይይት መድረኩ ባለሃብቶች እና የዘርፉ ተዋናንያን ታድመዋል። በከተማዋ የሚገኙ አምራቾችም ምርቶቻቸውን ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ እያስተዋወቁ ነው።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ግርማይ ልጅዓለም የኤግዚቢሽን እና ውይይት መድረኩ ዓላማ ጎንደር እና አካባቢው ያለውን የመልማት አቅም በማሳየት በጋራ ለመሥራት ነው ብለዋል፡፡ በውይይቱ ያሉ አቅሞችን እና ፀጋዎችን በማሳየት በውስንነቶች ላይ በመምከር የጋራ መፍትሔ መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው የምክክር መድረኩ የጎንደር እና አካባቢው የመልማት ሂደት የሚወሰንበት ነው ብለዋል፡፡ ጎንደር ሁለንተናዊ ዕድገት እና መልማት ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስፈልጋታል ነው ያሉት። ባለፋት አራት እና አምስት ዓመታት በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት አልሚ ባለሃብቶች ከተማዋን ለቅቀው እንደወጡም አስረድተዋል፡፡
“በችግሮቻችን ላይ ስለነቃን ሕዝብ እና መንግሥት ተቀራረበን እየሠራን ነው” ብለዋል። በዚህም ለውጦች መታየታቸውን አንስተዋል። ችግሮች እና ውስንነቶች የሉም አንልም ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተቀራርበን እንሠራለን፤ ልናገለግላችሁ ዝግጁዎችም ነን ብለዋል።
በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት በርካታ ችግሮች ሲፈጠሩ ጎንደር ውስጥ አንድም የኢንዱስትሪ ተቋም ጉዳት እንዳልደረሰበትም አብራርተዋል፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዱ የኢንዱስትሪ ተቋማትን ጠባቂው ሕዝቡ ራሱ ስለኾነ ነው ብለዋል። ነገም ሕዝብ ስለሚጠብቅ በኢንዱስትሪ ተቋሞች ላይ ምንም አይነት ችግር እንደማይፈጠር ማረጋገጥ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
ጎንደር ስትስቅ ብቻ ሳይኾን ስታነባም አብረን መቆም ይኖርብናል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በተለያዩ ችግሮች ከከተማ የወጡ አምራቾች እና አልሚ ባለሃብቶች ወደ ከተማቸው መጥተው በጋራ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
