
ባሕር ዳር: ጥር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ሥርዓት እና ኒውትሪሽን ሥራዎችን ቅንጅታዊ አሠራር ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል። የጤና እና ግብርና ሚኒስቴሮች በጋራ የሚያስተባብሩት 15 ሴክተር መሥሪያ ቤቶችን ያካተተው የምግብ ሥርዓት እና ኒውትሪሽን ጥምር የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ ነው ውይይት ያካሄደው። በሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም ፣ በኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን እና ኒውትሪሽን ሴክሬተሪያት የተሠሩ ሥራዎች እና የተገኙ ተሞክሮዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በጤና እና በግብርና ሚኒስትሮች እየታየ ያለው ቅንጅት እና ለውጤት የመሥራት ተነሳሽነት በጥሩ ደረጃ ላይ መኾኑን ገልጸዋል።
የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም ውጤታማነቱ የታየ፣ በፍጥነት ወደ ትግበራ በመግባት ለውጥ ያሳየ ፕሮግራም መኾኑንም ተናግረዋል። በሰቆጣ ቃል ኪዳን የተገኘው ተሞክሮ ወደ ሌሎችም ሰፍቶ ባጠረ ጊዜ ለተሻለ ውጤት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) እስካሁን የተሠሩ ሥራዎችና የተገኙ ስኬቶች አበረታች መኾናቸውን ገልጸዋል። ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የሚቀሩ ሥራዎችን በቀጣይ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ለበለጠ ውጤታማነት መሥራት አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
