የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ የመሬታቸውን ለምነት እየመለሰ መኾኑን የባንጃ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

37

እንጅባራ: ጥር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የ2017 ዓ.ም የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ በባንጃ ወረዳ ሰንከሳ ቀበሌ ተጀምሯል። የወረዳው አርሶ አደሮችም የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ከተጀመረ ወዲህ የመሬታቸው የአፈር ለምነት መመለሱን ተናግረዋል።

መሬት ትውልድ በቅብብሎሽ የሚጠበቀው ውድ የተፈጥሮ ሃብት ነው ያሉት አርሶ አደሮቹ ይህን ሃብት ተንከባክቦ የመያዝ፣ የመጠቀም እና ለትውልድ የማስተላለፍ አደራ እየተወጡ መኾናቸውን ገልጸዋል።የተራቆጠተ አካባቢን ለትውልድ እንደማያስተላልፉም ተናግረዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አዲሱ ስማቸው በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከጥር 15/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ አካባቢዎች በሚተገበረው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ 405 ተፋሰሶችን እንደሚሸፍን ተናግረዋል። ለዚህም የማልሚያ መሳሪያ ፣ አልሚ የሰው ኀይል ልየታ እና የካርታ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ነው የገለጹት።

የተፋሰሶችን ዘላቂነት በማረጋገጥ ረገድ በተከናወኑ ተግባራት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ 197 ተፋሰሶች በኅብረት ሥራ ማኅበራት ተካተው የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ እንደኾነም ገልጸዋል።

ለአንድ ወር በሚከናወነው የዘንድሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ከ232 ሺህ በላይ አልሚ የሰው ኀይል ይሳተፋልም ተብሏል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከተማችን የጋራ ቤታችን ናት” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next articleየተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራውን በተቀናጀ መንገድ ለመምራት እየተሠራ ነው፡፡