
ባሕር ዳር: ጥር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ባለሃብቶች እና የንግዱ ማኅበረሰብ የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው። ውይይቱ በቀጣይ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በሚከናወኑ ሕዝብን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ላይ ያተኮረ ነው።
በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የሚቆመው በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ ቅንጅት ነው ብለዋል። ባሕር ዳር ከተማ በአምራች ኢንዱስትዎች፣ በአገልግሎት እና በሌሎችም ማኅበራዊ ዘርፎች ባለሃብቶች ተሰማርተው እያለሙ የሚገኙባት ከተማ መኾኗን ገልጸዋል። ይህም ለከተማዋ እድገት እና ዘመናዊነት፣ ለነዋሪዎቿም ተጠቃሚነት ትልቅ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።
ባሕር ዳር ከተማ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ ናት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የኑሮ ውድነት እና ሥራ አጥነትን ለመቀነስም መጠነ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። በጋራ በመሥራት የተጀመሩ ሥራዎችን የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባልም ብለዋል።
“ከተማችን የጋራ ቤታችን ናት” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የጋራ ቤታችንን ለማልማት እና ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረጉ ሁሉም ሚናውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የከተማዋ ባለሃብቶችም እየተገነቡ ያሉ መሠረተ ልማቶች ሰው ተኮር ኾነው በቶሎ በሚጠናቀቁበት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ሀሳባቸውን አንስተዋል። ከውይይት በኋላም ልማቶችን እየተዘዋወሩ በማየት ተጨማሪ ሀሳብ እና አስተያየቶችን እንደሚሰጡ ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
