በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት እንደሚሠራ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።

52

ደብረ ማርቆስ: ጥር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር “ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ኢንቨስትመንትን እናስፋፋ” በሚል መሪ መልዕክት ከባለድርሻዎች አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል።

በመድረኩ የተሳተፉ በኢንቨስትመንት የተሠማሩ ባለሀብቶች ተቋማት ፍትሐዊ አገልግሎት በመስጠት የብድር አቅርቦት እና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።

በሥራ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን በማበረታታት እና ችግር ያለባቸውን በማስተካከል በከተማዋ ዘላቂ እና የተረጋጋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲኖር ተቀናጅተው እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ተመሥገን ተድላ በከተማዋ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች ፈቃድ ካገኙ 234 ፕሮጀክቶች መካከል 82ቱ ወደ ማምረት መግባታቸውን ገልጸዋል።

መድረኩ በጸጥታ ችግር ምክንያት የተቀዛቀዘውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት፣ ችግሮችን በጋራ በመፍታት አዳዲስ አልሚ ባለሃብቶችን ወደ አካባቢው ለመሳብ ዓላማ አድረጎ የተዘጋጀ መኾኑን ተናግረዋል።

በአካባቢው ለከተማዋ ዕድገት ወሳኝ አና ለአልሚዎች አዋጭ የኾኑ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊው ሰላም እንዲጸና እና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ተቀናጅቶ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ መሬት ወስደው ለማልማት ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶችን በቅንነት ለማገልገል እና የሚያነሷቸውን ችግሮች ቀርቦ ለመፍታት ከተማ አሥተዳደሩ ዝግጁ መኾኑን ገልጸዋል።

ለልማት የተላለፉ የኢንቨስትመንት ቦታዎች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ የክትትል እና ድጋፍ ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ባለሃብቶች ለከተማዋ ዕድገት እና ሰላም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጠይቀዋል።

በደብረ ማርቆስ ከተማ ለኢንዱስትሪ መንደር ከተዘጋጀው 1ሽ 200 ሄክታር መሬት ውስጥ 300 ሄክታር የሚኾነው ለአልሚዎች መተላለፉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቃና ዘገሊላ በጎንደር ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።
Next articleፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በጎንደር ከውጭ ሀገር ጎብኝዎች ጋር መገናኘታቸውን ገለጹ።