
ባሕር ዳር: ጥር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማጭበርበር የወንጀል ድርጊቶችን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ወንጀሎች ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል።
አገልግሎቱ በሰጠው መግለጫ የፋይናንስ ወንጀሎች በሀገር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ዘርፈ ብዙ በመኾኑ ኢትዮጵያ ወንጀሎቹን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተለያዩ ሕጎችን አውጥታ በመተግበር እንደምትገኝም አስገንዝቧል፡፡
በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 እየተተገበረ መኾኑ ይታወሳል ብሏል በመግለጫው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀድሞ በተለያዩ ሕጎች ውስጥ ተበታትነው የሚገኙ የሕግ ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ ራሱን የቻለ የንብረት ማስመለስ አዋጅ በቅርቡ መጽደቁን አስታውሷል፡፡
የንብረት ማስመለስ አዋጁም ኾነ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ አለያም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ዓላማ የፋይናንስ ወንጀሎች አትራፊ አለመኾናቸውን በማረጋገጥ በሀገር ላይ የሚያደርሰው ሁሉን አቀፍ አደጋ መግታት ነው ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ለጤናማ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥርም ነው ያስረዳው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ግለሰቦች ሕጎችን ለማደናገሪያነት በመጠቀም እንዲሁም የተለያዩ ተቋማትን ስም በመጥቀስ በማጭበርበር እና በማስፈራራት ገንዘብ ለማግኘት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መኾናቸውን ክትትል በማድረግ የተደረሰበት መኾኑን ገልጿል።
በዚህም በተደራጀ አግባብ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ውስጥ ሦስት ግለሰቦች ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም እጅ ከፍንጅ ተይዘው ጉዳዩ በምርመራ ላይ ይገኛል ብሏል፡፡ ሌሎችንም በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጸው፡፡
አገልግሎቱ ከራሱ ምንጮች እና ከጥቆማ በሚደርሱት መረጃዎች መሠረት የማጭበርበር የወንጀል ድርጊቶችን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ወንጀሎች ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሠራ ይገኛልም ብሏል።
በርካታ ጉዳዮችም በሕግ ተይዘው ይገኛሉ ያለው አገልግሎቱ የወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎች የሕግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አገልግሎቱ የሚወስዳቸውን ርምጃዎች የበለጠ አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።
ኅብረተሰቡም ማጭበርበርን ጨምሮ ሌሎች የፋይናንስ ወንጀል በመፈጸም የሚገኝን ገንዘብ ሕጋዊ ለማስመሰል የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ሲመለከት በ9796 ነፃ ስልክ ለፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በመደወል ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!