የሕዝብ ችግሮች በየደረጃው ባለው የመንግሥት መዋቅር እንዲፈቱ ይሠራል።

24

እንጅባራ: ጥር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ቡድን በእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር እየተሠሩ ያሉ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን የመስክ ምልከታ አካሂዷል።

የጤና ተቋማት፣ የቀበሌዎች አገልግሎት አሰጣጥ እና የከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ምልከታ ከተደረገባቸው መካከል ይገኙበታል። ቡድኑ በመስክ ምልከታ ግኝቶች እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ከከተማ አሥተዳደሩ ከተወጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋርም ውይይት አድርጓል።

የከተማው ነዋሪዎችም ከተማ የደረጃ ሽግግር፣ የኀይል አቅርቦት ማነስ፣ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር፣ የሕገወጥ ንግድ መበራከት፣ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ በወቅቱ አለመሰጠት፣ የመጽሐፍት አቅርቦት እና ሌሎችንም ሊፈቱላቸው የሚገቡ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የከተማ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ በላይ ዘለቀ ቡድኑ ባካሄደው የመስክ ምልከታ እና በተደረገው የሕዝብ ውይይት በከተማ አሥተዳደሩ በርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸው ሥራዎች በመሠራት ላይ መኾናቸውን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ሥራዎች የማኅበረሰቡ ተሳትፎ የሚበረታታ እንደኾነም አንስተዋል። በአንፃሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እና የሥራ ዕድል ፈጠራ በሚፈለገው ልክ አለመኾን መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች መኾናቸውን ገልጸዋል።

በተደረገው የመስክ ምልከታ እና በሕዝብ ውይይት የተነሱ ችግሮች በየደረጃው ባለው የመንግሥት መዋቅር እንዲፈቱ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቃና ዘገሊላ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደብረ ማርቆስ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።
Next article“የፋይናንስ ወንጀሎች ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ ነው” የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት