“ለአዕምሮ ሕሙማን በጤና ተቋማት ከሚሰጠው ሕክምና ባለፈ የማኅበረሰቡ እንክብካቤ ያስፈልጋል” የሥነ አዕምሮ ባለሙያ

35

ደብረ ማርቆስ: ጥር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ላይ በርካታሰዎች ለአዕምሮ ሕመም ተጋላጭ መኾናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል። በኢትዮጵያም የአዕምሮ ሕመም ችግር የሚያጋጥማቸው ወገኖች በርካቶች መኾናቸውን የጤና ሚኒስቴር ይገልጻል።

በደብረ ማርቆስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሥነ አዕምሮ ባለሙያ ዶክተር ማሩ ሙሉአዳም የአንድ ሰው የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴን በሥርዓት መወጣት አለመቻል፣ የማይጠበቁ የስሜት ለውጦች መኖር፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለው ተግባቦት ጤናማ አለመኾን እና ሌሎችም የስሜት ለውጦች የአዕምሮ ሕመም ተጠቂዎች ላይ የሚስተዋሉ ምልክቶች መኾናቸውን ተናግረዋል።

የአዕምሮ ሕመም መነሻ ምክንያት በትክክል ይሄነው ብሎ መናገር ባይቻልም በአዕምሮ ውሰጥ ያሉ ኬሚካሎች በሚዛቡበት ወይም የአንጎል ክፍሉ ላይ ጉዳት ሲደርስ ሊከሰት ይችላል ብለዋል።

የአዕምሮ ጤና እክል በማኅበራዊ ሕይወት የተመቸ ካለመኾን ጋር በተገናኘ ሊከሰት እንደሚችል የተናገሩት ባለሙያው ምቹ የሥራ አካባቢ አለመኖር፣ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ለዚህ ሕመም አጋላጭ ናቸው ይላሉ።

እንደ ዶክተር ማሩ ገለጻ ሕመሙ በሁሉም የዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ሰዎችን ሊያጠቃ የሚችል ይችላል። በአብዛኛው ከ15 እስከ 25 የዕድሜ ክልል እንዲሁም ከ65 ዓመት በላይ በኾኑ ሰዎች ላይ በስፋት ይከሰታል ነው ያሉት።

የአዕምሮ ሕመም እንደ ማንኛውም የጤና እክል ታክሞ መዳን የሚችል ሕመም ነው ያሉት ዶክተሩ የንግግር ሕክምና፣ የመድኃኒት ሕክምና እና የአኗኗር ዘይቤን የማስተካከል ሕክምና ይሰጣል ብለዋል።

በጤና ተቋማት ለአዕምሮ ሕሙማን ከሚሰጠው ሕክምና ባለፈ ማኅበረሰቡ ሕሙማንን በመንከባከብ ከሕመማቸው ሊፈውሳቸው የሚችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥር እንደሚገባ አመላክተዋል።

የአዕምሮ ጤናን ለመጠበቅ ማንኛውም የመንግሥት እና የግል መሥሪያ ቤቶች ለሠራተኞቻቸው ምቹ የኾነ የሥራ አካባቢን ሊፈጥሩ እንደሚገባም ባለሙያው መክረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአንድነት እና ፍቅር በጥምቀት
Next articleየቃና ዘገሊላ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደብረ ማርቆስ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።