ከ50 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የንጹሕ መጠጥ የውኃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።

36

ከሚሴ: ጥር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከ193 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ተመረቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጨፋ ሮቢት ከተማ፣ ባቲ እና ደዋ ጨፋ ወረዳዎች ከ50 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ናቸው ለአገልግሎት ክፍት የኾኑት።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ተደራሽነት ችግር መኖሩን ገልጸዋል። ግንባታቸው የተጠናቀቁት የውኃ ፕሮጀክቶች ሽፋኑን ከነበረው 45 በመቶ ወደ 60 በመቶ ያሳድገዋል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት እና ረጅ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ተደራሽነትን ለማሻሻል እየተሠራ ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡን በማሳተፍ የውኃ ፕሮጀክቶች እንዳይጓተቱ እና ለብልሹ አሠራር እንዳይጋለጡ ትኩረት መሰጠቱንም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ያደረጉት የኢፌዴሪ ውኃ እና ኢነርጅ ሚንስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ.ር) መንግሥት በሰሜኑ ጦርነት የተጎዱ እና እርጥበት አጠር በኾኑ አካበቢዎችን የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ተናገረዋል።

የክልሉ መንግሥት የማኅበረሰቡን የልማት ችግር ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በልማቱ ላይ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ለሌሎች አካባቢዎችም ተሞክሮ የሚወሰድበት መኾኑን አንስተዋል። በተመረቁት የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተጠቃሚ የኾኑ የአካባቢው ነዋሪዎችም ምስጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ባለ ዓለምዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቃና ዘገሊላ ውኃ ወደ ወይን የተቀየረበት።
Next articleአንድነት እና ፍቅር በጥምቀት