
ባሕር ዳር: ጥር 12/2017 ዓ.ም ( አሚኮ) ቃና ዘገሊላ በየዓመቱ ጥር 12 በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው። ቃና ዘገሊላ የሚሉት ሁለት ቃላት ተነጣጥለው የሚነበቡ እንደኾነ ሃይማኖታዊ አስተምህሮው ያስረዳል።
ገሊላ በእስራኤል እና በፍልስጤም አካባቢ የምትገኝ የአውራጃ ስም ስትኾን ቃና ደግሞ በገሊላ ውስጥ የምትገኝ ሰፈር ስም ናት ይላሉ የትርጓሜ መምህሩ መምህር ዘላለም በላይ።
ቃና ዘገሊላ በቀጥታ ትርጉሙ የገሊላዋ ቃና ማለት ነው ብለዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ጥምቀት በተከበረበት ማግስት ጥር 12 ቀን የቃና ዘገሊላ ክብረ በዓል ይከበራል፡፡
ይህ በዓል ከኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ የሚከበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዳራ ያለው በድምቀት የሚከበር በዓል ነው ይላሉ መምህር ዘላለም፡፡ በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ ክፍል በኸነችው ቃና በተባለቸው ሰፈር በፈጸመው ተዓምር እንደኾነ ሃይማኖታዊ አስተምሮው ያትታል፡፡
ይህ በዓል ምንን ለማሰብ የሚከበር ነው ያሉ እንደኾነ ይላሉ መምህር ዘላለም ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ ክፍል በምትገኝ ቃና ላይ በተደረገ የዶኪማስ ሰርግ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም እና ከደቀ መዛሙርቶቹ ጋር ተገኝቶ ነበር፡፡ ምግቡ፣ መጠጡ ለሰርጉ ታዳሚየን መታደል ጀመረ፤ በመካከል ሰርገኞቹ ወይን አለቀባቸው፡፡ መቼም እንግዳ ተጠርቶ፣ ደግሱ ሲያልቅ ያስጨንቃል።
በዚህም ሰርገኛው እጅግ ደነገጠ። አፈረም። በዚህ ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇና ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ በኃይሉ የዚህን ሰው ጭንቀት ያርቅለት ዘንድ ጠየቀችው። ልጇም የእናቱን ምልጃ ተቀበለ።
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ በረከት የሞላበት ተዓምር ሠራ ይላሉ መምህር ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሠርገኞች በጋኖቹ ላይ ውኃ እንዲሞሉ አዘዛቸው።
ሠርገኞችም ጌታ ያላቸውን አደረጉ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም በኃይሉ ውኃውን ወደ ወይን ቀየረው። ቃና ዘገሊላ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃውን ወደ ወይን የቀየረበት፣ ተዓምር የሠራበትን ቀን የምናስብበት በዓል ነው ይላሉ መምህሩ።
የጌታን ተዓምር ያዩ ሁሉ ተደነቁ። ሠርገኞችም ተደሰቱ። ያለቀውን ድግስ መላ። ይህችም ቀን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ በጥር 12 ቀን በድምቀት ትከበራለች። ጥምቀት በዋለ በማግስቱ ጥር 12 የቅዱስ ሚካኤል በዓል ነው።
ታቦታቱ ለጥምቀት በዓል ጥር 10 ወደ ባሕረ ጥምቀት ይወርዳሉ። በጥምቀተ ባሕሩ አድረው። ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ይፈጸማል። በጥር 11 ታቦታቱ በታላቅ አጀብ እንደወረዱ ሁሉ በታላቅ አጀብ ወደ መንበረ ክብራቸው ይመለሳሉ። የቅዱስ ሚካኤል ታቦት ግን በዚያው በጥምቀተ ባሕሩ ያድራል።
ወደ መንበረ ክብሩም የሚመለሰውም በጥር 12 ቀን የቃና ዘገሊላ ነው። ታዲያ የቅዱስ ሚካኤል ታቦት በዚሁ ቀን ወደ መንበረ ክብሩ የሚመለስበት ነውና ምዕመናን በተለምዶ የሚካኤል የጥምቅት እያሉ ይጠሩታል ነው የሚሉት መምህሩ። በዓሉ ግን የቃና ዘገሊላ ነው የሚሉት።
የቃና ዘገሊላ በኢትዮጵያ በታላቅ ድምቀት ይከበራል። ምዕምናን የጌታቸውን ተዓምር ያስባሉ። ለጌታቸውም ምስጋና ያቀርባሉ። በጥምቀተ ባሕር ተገኝተው የቅዱስ ሚካኤልን
ታቦት ያጅባሉ። ሊቃውንቱ ይዘምራሉ። በታላቅ አጀብም የቅዱስ ሚካኤልን ታቦት አጅበው ወደ መንበረ ክብሩ ያስገባሉ። ይህ በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባለፈ ታላቅ ባሕላዊ ክዋኔዎች የሚከወኑበት ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!