“ትሕትና የልዕልና መሠረት ነው” መጋቢ ሀዲስ መምህር ዜናዊ አሸተ

58

ሁመራ: ጥር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሁመራ ከተማ የጥምቀት በዓል በተከዜ ወንዝ ዳርቻ ተከብሯል። የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ በአደባባይ ሥርዓታቸው ከሚፈጸሙና ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ ነው።

የጥምቀት በዓል ልክ እንደሌሎቹ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በዓላት ሁሉ ሃይማኖታዊ ባሕል፣ ትውፊትና ሥርዓት ያለው ሲሆን በባሕር አልያም በወንዝ ዳርቻዎች መከበሩም ለዚህ ምስክር ነው።

በሃይማኖቱ አስተምህሮ የጥምቀት በዓል ታሪካዊ መሰረቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ባሕር ሄዶ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ መጠመቁ ነው።

“ትሕትና የልዕልና መሠረት ነው፤ ትዕቢት ውድቀትን ትቀድማለች፤ ክርስቶስም ሲጠመቅ ይህንን አስተምሮናል” ሲሉ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቢ ሀዲስ መምህር ዜናዊ አሸተ ገልጸዋል።

ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ባሕር ሄዶ የተጠመቀው አንድም የሰውን ልጅ የዕዳ ደብዳቤ ለመቅደድ፤ አንድም ራስን ዝቅ በማድረግ ከፍ ማለትን ለሰው ልጅ ሁሉ ለማስተማር ነው ብለዋል። ሁላችንም በትህትና ዝቅ ስንል ራሳችን ከፍ ብሎ እናገኘዋለን ሲሉ ገልጸዋል።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሐንስን እርሱ ወዳለበት ጠርቶ አጥምቀኝ ያላለው ለሰው ልጅ ሁሉ ሕግ ሊሠራለት ፈልጎ ነው፤ እንዲህ ባይሆን ኖሩ ክርስቶስ ወደ ዮሐንስ ከሚሄድ ዮሐንስ ወደ ክርስቶስ ቢሄድ ይቀል ነበር ሲሉ የትህትናን እና የሥርዓቱን ምሥጢር አስረድተዋል።

በሀብት፣ በሥልጣን፣ በዕውቅና፣ በዘመድ ብዛትም ቢሆን ከፍ ያለ ንጉሥ ወይም ሕዝብ ቢኖር ከፍ ከፍ ማለትን ካሻ ራሱን ዝቅ ዝቅ አድርጎ የክርስቶስን ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም መጋቢ ሀዲስ አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

“እኛ በተከዜ የወንዝ ዳርቻ ጥምቀትን ማክበራችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ባሕር ተጠምቆ ስላሳየን ነው” ያሉት ደግሞ የሁመራ ከተማ ከንቲባ አለሙ ከየነው ናቸው።

ከለውጡና ከነጻነት በኋላ በተከዜ ወንዝ ዳርቻ ጥምቀትን ስናከብር ለሁለተኛ ጊዜ ነው፤ በዚህም ሕዝቡ ሃይማኖቱንና ማንነቱን በደስታ እየገለጠ ነው ብለዋ ከንቲባው።

ወደፊትም ጥምቀትን በተከዜ ዳርቻ ማክበራችን ይቀጥላል ያሉት ከንቲባው ይህም የወሰንና የማንነታቸን መሠረት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን፣ ባሕልና ወጉን ፣ አማራዊ ማንነቱንም በደስታ የገለጠበት ደማቅ በዓል መሆኑን አቶ አለሙ ገልጸዋል። በቋንቋው፣ በባሕሉ፣ በማንነቱ ኮርቶ በዓሉን ሲያከብር ትልቅ የደስታ ስሜት ፈጥሮለታ ነው ያሉት።

እንዲህ ዓይነት ደማቅ የጥምቀት በዓል በሁመራ ዐይቼ አላውቅም ያሉት ከንቲባው የዛሬው ጥምቀት የጎንደርን ይመስላል ሲሉ የተከዜውን ድባብ ገልጸውታል።

ዛሬ ያከበርነው የጥምቀት በዓል ከኢሱስ ክርስቶስ የተግባር ትሕትና የወረስንበት ነው ስትል የበዓሉ ተካፋይ በለጡ አበራ ገልጻለች። በዓሉን በተከዜ ዳርቻ ማክበራችን ልዩ ደስታ ፈጥሮልናል ነው ያለችው።

ሌላው የበዓሉ ታዳሚ ገሠሠው ወንድም (ዶ.ር) የጥምቀት በዓል ከዘጠናዎቹ ጀምሮ ተከዜን በመተው በከተማው መሃል ይከበር እንደነበር በማውሳት ከነጻነት ማግስት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ግን ወደ ጥንታዊ ቦታው ተመልሶ በተከዜ ዳርቻ መከበር ጀምሯል ሲሉ ተናግረዋል።

ዶክተር ገሠሠው አክለውም የተከዜን ዳርቻ እንደ ዮርዳኖስ ሆኖ አግኝተነዋል ያሉ ሲሆን ይሄም ልዩ የደስታ ስሜትን እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ሥርዓተ ጥምቀቱ በንጋት ተጀምሮ የተጠናቀቀ ሲሆን ታቦታቱ ከተከዜ ማረፊያቸው በዝማሬ፣ በዝማሜ፣ በዕልልታና በሆታ ወደየአድባራት መንበራቸው ተመልሰዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሁላችንም ለሀገር ሰላም እና ዕድገት የሚጠበቅብንን ልንወጣ ይገባል” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
Next article“በዓሉን ስናከብር ከመነቃቀፍ ይልቅ በመተቃቀፍ ከመለያየት ይልቅ በአንድነት ሊኾን ይገባል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት