“ጥምቀት ሁላችንም በፍቅር እና በትህትና እንድንኖር ያስተምራል” አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ

30

ባሕርዳር: ጥር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በቅዱስ ላሊበላ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

በበዓሉ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም አሥተዳዳሪ አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ፣ የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክንያት ከንቲባ ወንድምነው ወዳጅን ጨምሮ ሊቃውንት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን፣ ምዕምናን እና የውጭ ሀገር እንግዶች ተገኝተዋል።

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም አሥተዳዳሪ አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ ጥምቀት ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወርዶ የተጠመቀበት እና ትህትናን ያስተማረበት ነው ብለዋል። ዮርዳኖስ ትህትና ታይቶባታል፣ በዮርዳኖስ የሰው ልጆች የዕዳ ደብዳቤ ተቀድዷል፣ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጎ ትህትናን አሳይቶናል ነው ያሉት። ጥምቀት ሁላችንም በፍቅር እንድንኖር ያስተምራል፣ጥምቀት የፍቅር እና የትህትና በዓል ነው ብለዋል።

የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክንትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጅ የጥምቀት በዓል አከባበር ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይኾን ባሕላዊም ይዘት ያለው መኾኑን ገልጸዋል።
ጥምቀት በርካታ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች እንዳሉትም ተናግረዋል።

በጥምቀት በዓል የተለያዩ ባሕላዊ ክዋኔዎች የሚካሄዱበት፣ ሕዝቡ ከልብ የመነጨ ደስታን የሚገልጽበት እና ማኅበራዊ መስተጋብሩን የሚያጠናክርበት ነው ብለዋል። በዓሉን በባሕላዊ አልባሳት በመድመቅ ማክበር የሀገር ገጽታን ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሚያስተዋውቅ መኾኑንም አመላክተዋል።

የጥምቀት በዓል በላሊበላ በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ይከበራል። ከላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ኮምዩንኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ጥምቀት በላሊበላ የበርካታ ጎብኝዎችን ቀልብ ይስባል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓለም የጥምቀት በዓልን እያከበረች ነው
Next article“የጥምቀት በዓልን ስናከብር ፍቅርን፣ ለሀገር ሰላም እና አንድነት መትጋትን በተግባር በማሳየት መኾን አለበት” ብፁዕ አቡነ በርቶሎሚዎስ