
ባሕር ዳር፡ ጥር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ላይ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ አማኞችን አቅፎ በያዘው የክርስትና ሃይማኖት የጥምቀት በዓል በተለያየ መልክ እና ቅርጽ እየተከበረ ነው።
ዓለም የጥምቀት በዓልን ስታከብር በሁለት ጎራ ተከፍላ ነው፤ የምሥራቅ እና የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት በሚል።
የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የሩሲያ፣ የአርመን፣ የዩክሬን፣ የሶሪያ፣ የግሪክ፣ የግብጽ እና ሌሎች መሰል የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን የያዘ ነው።
የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉት ደግሞ የሮም ካቶሊካዊት፣ የሉተራን እና አንጀሊካን አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።
ታዲያ በእነዚህ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት እና አማኞቻቸው ዘንድ የጥምቀት በዓል አከባበሩ ለየቅል ነው።
የምዕራቡ አብያተ ክርስቲያናት የጥምቀት በዓልን የሚያከብሩት ከኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ጋር ተያይዞ ሰብአ ሰገል ኢየሱስ ክርስቶስ ወደተወለደባት ከተማ ቤተልሄም ያደረጉትን ጉዞ እና ያቀረቡት ሥጦታ በማስታወስ ሲኾን በምሥራቁ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ባሕር በቅዱስ ዮሐንስ መጠመቁን በማመን እና በማስታወስ ነው።
በምዕራቡ አብያተ ክርስቲያናት እና አማኞች ዘንድ ከገና በዓል ጋር አያይዘው የጥምቀት በዓልንም ከሳምንት በፊት አክብረዋል። በምሥራቁ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ የጥምቀት በዓል ጥር 11 ይከበራል።
በእንግሊዝ ያሉ አማኞች ደግሞ የገና ሰሞን መሰናበቻን 12ኛውን ቀን 12ኛው ምሽት በሚል የጥምቀትን በዓል በድግስ ያከብሩታል። በስፔን፣ በፊሊፕንስ እና በደቡብ አሜሪካ ሀገራት ‘’ኤል ዲያ ዲ ሎስ ሬዬስ ማጎስ’’ ይሉታል የጥምቀት በዓልን በስፓኒሽ ቋንቋ።
ይሄን ማለታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱን የሰሙት ሰብአ ሰገል ለሥጦታ ያዘጋጁትን ወርቅ፣ እጣን እና ከርቤ በፈረስ እና ግመል ጭነው ሕጻኑን ኢየሱስ ክርስቶስ ለማየት ወደ ቤተልሄም ከተማ መሄዳቸውን የሚገልጽ ነው የቃሉ ትርጓሜ።
በእነዚህ ሀገራት የጥምቀት በዓል ሲከበር በተለይም ሰብአ ሰገልን የሚወክሉ አዛውንቶች ወይም በእነሱ አጠራር ‘ሳንታ ክላውስ’’ ለልጆች ሥጦታዎችን በማበርከት ነው።
እንደሜክሲኮ ባሉ ሀገራት ደግሞ ሮስካ ዲ ሪዬስ በተባለው ተወዳጅ እና ጣፋጭ ኬክ በሕጻን ምስል በመሥራት በአደባባይ የጥምቀት በዓልን ያከብሩታል።
በሕጻን ምስል የተዘጋጀው ኬክ የኢየሱስ ክርሰቶስን መወለድ ለማመላከት ነው ይላሉ ሜክስኳውያን። በኢትዮጵያ፣ በግሪክ፣ በቆጵሮስ፣ በአርመን፣ በሶርያ፣ በኤርትራ፣ በቡልጋርያ፣ በግብጽ፣ በዩክሬን፣በሩስያ እና በሌሎች የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የጥምቀት በዓል ጥር 11 የሚከበር ሲኾን ሀገራቱን አንድ የሚያደርጋቸው ጉዳይ የኢየሱስ ክርስቶስን በዮርዳኖስ ባሕር መጠመቁን በማስታወስ በዓሉን ማክበራቸው ነው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ ሀገራት የጥምቀት በዓልን በአደባባይ ያከብራሉ፤ ጥቂቶች ደግሞ በአብያተ ክርስቲያናት አጥር ግቢ ያከብራሉ። ሁሉም የኦርቶዶክስ አማኞች የኢየሱስ ክርስቶስን መጠመቅ በማስታወስ እና በመጠመቅ በዓሉን ያከብራሉ።
የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር የሚጠቀሙት አማኞች የጥምቀት በዓል የአዲስ ዓመት ሰሞን በመኾኑ መጠመቃቸው ዘመኑ የተባረከ እንደሚኾንላቸውም ያምናሉ።
እንደ ሩሲያ ያሉ የኦርቶዶክስ አማኞች በካህናት በተባረከ በረዷማ ውኃ ውስጥ ራሳቸውን ሦሥት ጊዜ በማጥለቅ ይጠመቃሉ፤ ጥምቀቱ የሠሩትን ሐጥያታቸውን እንደሚሽር እና በመንፈስ እንደገና እንደተወለዱ እንደሚያደርጋቸው ያምናሉ።
ያም ኾነ ይህም ግን፣ ይብዛም ይነስም፣ እንደ ባሕል እና ዕምነቱ ዓለም የጥምቀትን በዓል በድምቀት እያከበረች ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!