
ደብረ ታቦር:ጥር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በደብረ ታቦር ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።
በበዓሉ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ሚካኤል፣ የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን፣ ሊቃውንት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ምዕምናን ተገኝተዋል።
የደብረ ታቦር መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የአራቱ ጉባዔያት መምህር መምህረ መምህራን የኔታ በጽሐ ዓለሙ ጥምቀት የቅድስት የሥላሴ አንድነት እና ሦስትነት የተገለጠበት በዓል ነው ብለዋል። ምድር ባዶ ኾና ነበር፤ ጨለማም ነግሶ ነበር፣ በጥምቀት ግን ብርሃን ተሰጥቷል ነው ያሉት።
ውኃ ዝቅ ያለውን ቦታ በመያዙ በዓለም ብዙ ቦታ ሊይዝ ችሏል ያሉት መምህረ መምህራን በጽሐ ትህትናን ከውኃ በመማር እኛ ዝቅ ብለን ብዙ ቦታ እንድንይዝ አስተማረን ብለዋል።
ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ ረቂቅ የነበረውን አንድነት እና ሦስትነት በገሀድ መግለጹንም ተናግረዋል። እኛም ከጥምቀት ሥነ ሥርዓቱ ትህትናን ልንማር ይገባል ብለዋል።
“ክርስቶስ ይችን ዕለት ሲሰጠን እና ስንጠመቅ የዕዳ ደብዳቤያችንን ቀድዶልናል። እኛ ሰዎች መጥፎ ነገር በመሥራት በራሳችን ላይ ዕዳ ማምጣት የለብንም” ነው ያሉት መምህሩ።
በበዓሉ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ ሚካኤል ቡራኬ አድርገዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!