የጥምቀት በዓል በኮምቦልቻ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

21

ደሴ: ጥር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ካህናቱ ሌሊቱን ሲያመሰግኑ እና ዕለቱን የተመለከተ ትምህርት ለሕዝቡ ሲያስተምሩ ነው ያደሩት፡፡

ከጠዋት 12 ሠዓት ጀምሮ የጥምቀተ ባሕሩ ጸሎት ከተደረገ እና ከተባረከ በኋላ በዓሉን ለማክበር ለተሰበሰበው ሕዝብ ተረጭቷል፡፡ ካህናቱ ሕዝቡን ጸበል ከረጩ በኋላ ልዩ ልዩ ያሬዳዊ ሥርዓቶች ፈጸመዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እና በከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች መልዕክቶች ከተላለፉ በኋላ ታቦታቱ ከድንኳናቸው ወጥተው በየአጥቢያቸው ወደ የመጡበት መንበራቸው በምእመናን ሆታና እልልታ፣ በካህናት ያሬዳዊ ዝማሬ ታጅበው እየተሸኙ ነው።

በበዓሉ ላይ ያነጋገርናቸው ወጣቶች የታቦታቱን ማለፊያ እና የሚያረፉበትን ቦታ በማፅዳት፣ ሰላሙን በማስጠበቅ በኩል ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ፣ የቃሉ እና አርጎባ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አሥኪያጅ ሊቀ ትጉኃን ሰለሞን አሰፋ ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መሄዱ የሰው ልጅ ከመንፈስ ቅዱስ መወለዱን ሊያረጋግጥልን ነው ይላሉ።

ጥምቀቱም አንድነት ሦስትነት የተገለጠበት እና የሐጢያት ደብዳቤ የተደመሰሰበት ዕለት መኾኑን ተናግረዋል።

ሊቀ ትጉኃን ሰለሞን አሰፋ አክለውም ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጡሩ በዮሐንስ እጅ መጠመቁም ፍጹም ትህትናን እንማርበታለን ነው ያሉት።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወንድወሰን ልሳነ ወርቅ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ማኅበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ማኅበረሰቡ የሰላሙ ባለቤት በመኾኑ ለሰላሙ መጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ለሃይማኖቱ ተከታዮችም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።

በዓሉ በደመቀ ኹኔታ በሰላም እየተከበረ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article” ጥምቀት ለኢትዮጵያዊያን ትልቁ መገለጫችን ነው” የደብረ ታቦር ከተማ ከንቲባ ደሴ መኮንን
Next article” እኛ ሰዎች መጥፎ ነገር በመሥራት በራሳችን ላይ ዕዳ ማምጣት የለብንም” መምህረ መምህራን የኔታ በጽሐ ዓለሙ