አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የተላከ መልዕክት ለዩጋንዳ እና ለኬኒያ ፕሬዚዳንቶች አደረሱ።

17

ባሕር ዳር: ጥር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የተላከ መልዕክት ለዩጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሰቬኒ እንዲሁም ለኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ አድርሰዋል፡፡

አምባሳደሩ ሬድዋን ሁለቱ መሪዎች መልካም ጉርብትና እና ቀጣናዊ ትብበር እንዲጠናከር ለተጫወቱት በጎ ሚና እንዲሁም ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ላሳዩት ቀናዒነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቶቹ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር እንዲሁም በራሷ አቅም በሶማሊያ እና በሌሎች ሀገራት ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ያበረከተችውን አይተኬ ሚና አውስተዋል፡፡

ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመጫወት ለይ ያሉትን ጉልህ ሚና አድንቀዋል፡፡ በቀጣይም ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሽብርተኝነትን በማዋጋት ረገድ የሚኖራትን ወሳኝ ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማጎልበት እና በኢትዮጵያ ሰላም እና ብልፅግና እንዲሰፍን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በማድረግ ላይ ያሉት ጥረት እንደሚደግፉ አስታውቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ የሀገሪቱ የፀጥታ እና ደህንነት ተቋማት ለኢትዮጵያ አቻዎቻቸው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ መመሪያ መስጠታቸውን ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለአሚኮ በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ረጅም ዓመት ያገለገሉ አባቶች የታሰቡበት መኾኑ ለየት ያደርገዋል” መልዓከ ገነት ደጀን ተስፋዬ
Next article” ጥምቀት ለኢትዮጵያዊያን ትልቁ መገለጫችን ነው” የደብረ ታቦር ከተማ ከንቲባ ደሴ መኮንን