
ባሕር ዳር: ጥር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በከሚሴ ከተማ የጥምቀት በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው።
የወረዳ አጥቢያዎች ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ መምህር ኤፍሬም መላኩ የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ የዮሐንስን ልዕልና እና የሱን ትህትና ያሳየበት በዓል እንደመኾኑ የሰው ልጆች ትህትናን ከክርስቶስ ሊማሩ ይገባል ብለዋል።
በዓሉ ሕዝበ ክርስቲያኑ ለሰላም ከፍተኛ ዋጋ የሰጡበት መኾኑንም ተናግረዋል። በበዓለ ጥምቀቱ አባቶች ለከፈሉት ዋጋ ማመስገን እና ለተተኪዎችም አርአያ መኾንን ታሳቢ ያደረገ ከ40 ዓመታት በላይ ላገለገሉ አባቶቸ ስጦታ የማበርከት መርሐ ግብርም ተከናውኗል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልዓከ ገነት ደጀን ተስፋዬ የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ አባቶች የታሰቡበት እና የተዘከሩበት መኾኑ ለየት ያደርገዋል ነው ያሉት።
የሰው ልጆች የክርስቶስን ትህትና እና አረአያ በመከተል በዓሉን ማክበር ይገባቸዋልም ብለዋል። መረጃው የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!