
ባሕር ዳር: ጥር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በጎንደር በድምቀት እየተከበረ ነው። በበዓሉ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳት እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የጥምቀት በዓልን ስናከብር በቅድሚያ የምንሰጠው ለሀገራችን እና ለሕዝባችን ሰላም ማወጅ ነው ብለዋል። የጥምቀት በዓል ከመሠረቱ የሰላም ነጋሪት የታወጀበት፣ የፍቅር እምቢልታ የተነፋበት፣ የሰው ልጆች የሕይዎት ጽልመትን ቋጥሮ የኖረው የዕዳ ደብዳቤ የተቀደደበት፣ የሰላም፣ የፍቅር እና የትህትና በዓል ነው ብለዋል።
በዓሉ ከበዓላት ሁሉ ለየት የሚያደርገው ፈጣሪ በፍጡሩ እጅ የተጠመቀበት እና ለትህትና እና ለፍቅር፣ ለዕውነት መገዛት ጠቃሚ መኾኑን የሚያጠይቅ በመኾኑ ነው ብለዋል። በጎንደር ነገሥታቱ እና መኳንንቱ የጌታ ትህትና የተገለጠበትን የጥምቀት በዓልን በአንድነት ያከብሩት እንደነበር አስታውሰዋል።
እኛም የአባቶቻችን አደራ ተቀብለን ለማስቀጠል እየሠራን ነው ብለዋል። ጎንደር በታሪኳ ልክ እንድታገኝ የሚያደርጓት የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ለዘመናት ተዘግታ ለኖረችው፣ የነገሥታት ከተማ ለኾነችው ውዷ ከተማችን ጎንደር እና አካባቢው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለሰጧት ትኩረት እናመሠግናለን ነው ያሉት።
እናትዋ ጎንደር የኢትዮጵያችን ድርና ማግ፣ የባሕላችን እና የታሪካችን ስንዱ እና እመቤት መኾኗንም ገልጸዋል። አሁን ላይ በአንዲት እናት ልጆች የተጫረው እሳት ለእርስ በእርስ መጠፋፋት ምክንያት ኾኖ መቀጠሉ እንደ መሪ ያሳዝነኛል ብለዋል።
አሁን ያለው ችግር ሁሉንም እንደሚያሳዝን እምነት አለኝ ብለዋል። በሕዝብ ስም እየማሉ የሕዝብን ሰላም የሚያደፈርሱ ኀይሎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ንጹሐንን የሚገድሉ፣ የሚያግቱ እና በዘረፋ የተሰማሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ይህ ድርጊት ክልሉን ወደኃላ ይጎትት ካልኾነ በስተቀር ፋይዳ የለውም ነው ያሉት።
ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደፍጡሩ እንደሄደ ሁሉ እኛም ወደ ወገኖቻችን በመሄድ ሰላም እና ፍቅር ልናስተምር ይገባል ብለዋል። የተሳሳተ አማራጭ በመከተል ሕዝቡን ባለ እዳ ማድረግ አይገባም ነው ያሉት። ለጎንደር የሚገባት፣ ዘላቂ ሰላም፣ አብሮነት እና ልማት ነውም ብለዋል።
ነዋሪዎቿን እግር ከወርች የሚያስር የዕዳ ደብዳቤ አያስፈልጋትም ነው ያሉት። ጎንደር እና አካባቢዋ ለታሪኳ እና ለእምቅ ሃብቷ የሚመጥን ልማት እንደሚያስፈልጋትም አስገንዝበዋል።
በየድርሻችን ሰላምን እንስበክ ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የሰላምን ጥሪ እናስተገባ ነው ያሉት። ልጆቿ ለሰላም እና ደኅንነቷ የሚሠሩላት ሊኾን እንደሚገባም አብራርተዋል።
ጦርነት እና ግጭት ኋላቀር እንደኾነ መገንዘብ እንደሚገባም ተናግረዋል። በመንግሥት በኩል ሰላማዊ አማራጮች ዛሬም እንዳልታጠፉ ገልጸዋል። የጥምቀት በዓል በድምቀት እንዲከበር ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!