“ጥርን ናፍቀን፣ በጥር ደግሰን፣ በጥር የምናምር የመናገሻዋ ከተማ ነዋሪዎች ነን” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው

13

ባሕር ዳር: ጥር 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በጎንደር በድምቀት እየተከበረ ነው። በበዓሉ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳት እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በበዓሉ መልዕክት ያሰተላለፉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር የጥር ሙሽራ ናት ብለዋል፡፡ ከንቲባው ጥርን ናፍቀን በጥር ደግሰን በጥር የምናምር የመናገሻዋ ከተማ ነዋሪዎች ነን ነው ያሉት፡፡ ጥምቀት በጎንደር መገለጫ ኾኖ የኖረ አንድ እሴት ስለመኾኑም ተናግረዋል።

ጎንደር የቱሪዝም ምልክት እና ከመላው ዓለም ቱሪስቶችን የሳበ ድንቅ ስፍራ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡ በዓሉ ጎንደር ለመላው ዓለም የሰጠችው እና ዓለምም የሰጣት ድንቅ ክስተት ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡

በውጭ እና በሀገር ውስጥ ኾነው ለጎንደር ልማት እየተጉ ላሉ ምሥጋና ያቀረቡት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጎንደር አሁንም መልማት የምትፈልግ እና እየለማች እና እያበበች ያለች ከተማ እንደኾነችም አስረድተዋል፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር አሁንም መልማት እንደምትፈልግ ነው የተናገሩት፡፡

ጎንደር አተገፍታ ስለቆየች አሁንም መልማት የምትሻ ናት ብለዋል። ተገፍታ የቆየችበትን ያንን ያለፈ ጊዜ በቁጭት ሠርታ ለማሳየት እየሠራች መኾኗንም አንስተዋል፡፡ ጎንደር በጅምር የልማት ጉዞ ላይ ብትኾንም አሁንም በዚህ ጊዜ መድመቋን ነው ያስገነዘቡት፡፡

ለሀገሪቱ ሕዝብም ኾነ ለክልሉ ሕዝብ ከመቸውም ጊዜ በላይ መናገር የምፈልገው ጎንደር ልማቷን እያስቀጠለች በልጆቿ ብርታት ሰላሟን እንደምታስጠብቅ እና ለሀገርም ሰላምን እንደምትሰጥ ነው ብለዋል። ሕዝቡም ለዚህ የቆመ እና ፊቱን ወደ ልማት ያዞረ ስለመኾኑ ነው ያብራሩት፡፡

ጎንደር ለምታለች እየለማችም ነው ሲባል በሩቅ ላላችሁ ፕሮፖጋንዳ ሳይኾን በተጨባጭ የሚታይ በመኾኑ ሁሉም በአካል ተገኝተው እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

ካልተገዳደልን ይልቁንም ከተደጋገፍን ሀገርን በልማት ከፍ እንደምናደርግ ምልክቱን አሳይተናል ነው ያሉት፡፡ ጥምቀት የትህትና በዓል በመኾኑ ዛሬም ሕዝቡ በትህትና ፍቅርን እንዲሰብክ እና ሁሌም ለሰላም እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

ሕዝቡ መሪው ሲያጠፋ መምከር እና መመለስ እንደሚገባው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ገልጸዋል። መሪው ለዚህ ዝግጁ እና ስሪቱ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡

መገዳደል እንዲቀር አብረን ምክረን በፍቅር ለመኖር ዝግጁ ነን ያሉት አቶ ቻላቸው ሁሉም ለዚህ እንዲዘጋጅ ጠይቀዋል፡፡

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
Next article“የጎንደር የተሐድሶ ዘመን ዛሬ ነው” ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ