የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

31

ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው ትህትናን ለማስተማር ነው። በመሆኑም ወደ አገልጋዩ ቅዱስ ዮሐንስ በመሄድ ራሱን ዝቅ አድርጎ መቅረቡ ትህትናን ለማስተማር መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ስለሆነም በኛ መካከል ትግስት መከባበር፣ መደጋገፍ፣ በአብሮነትና ትህትና ልንላበስ ይገባል።

ሌላኛው ኢየሱስ የተጠመቀበት ምክንያት አርዓያ ለመሆን ነው። ሰው ሁኖ በምድር ሲመላለስ እንደአምላክነቱ ለማዳን ሰው እንደመሆኑ ደግሞ አረያ ለመሆን ነው። እኛ ኢትዮጵያውን ለልጆቻችን መልካም ነገርን ኢትዮጵያዊ ቀለምን ሕብረብሔራዊነትን እህታማችነትንና ወንድማማችነትን በመስበክ ከአምላካችን የወስድነውን አርዓያነት ልንፈፅም ይገባናል።

ሦስተኛው ኢየሱስ የተጠመቀበት ምክንያት የሰው ልጆችን የእዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ ነው። የሰው ልጅ በጥፋቱ ከገነት ተባሮ በዲያቢሎስ ቀንበር ስር በነበረበት ወቅት እንደሰውነቱ ተገርፎ ተረግጦ እንደአምላክነቱ አቅልጦ አድኖናል።

ግን ዛሬም ምድራችን የግፍ ፅዋ ሞልቶ እየፈሰሰባት ነው። ወንድም ወንድሙ እየገደለ ነው። ከዚህ አስከፊና ኋላቀር የመጠፋፋት አባዜ መውጣት ይኖርብናል።

እኛ የአንዲት አገር ልጆች ነን። ተነጋግረን መግባባትን ተወቃቅሰን መማማርን ባህል ማድረግ አለብን። ዛሬም የሞት ሞት ለመሞት መጠፋፋት የለብንም።

አራተኛው የመጠመቅ ምክንያት መገለጥ ሲሆን በስላሴ አንድነትና ሦስትነት የተገለጠበት ነው። ይህም እግዚአብሔር ወልድ እንደ አንድ የ30 ዓመት ጎልማሳ ሁኖ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በእርግብ አምሳል በእሱ ላይ ወርዶ ሲታይ እግዚአብሔር አብ ደግሞ በደመና ሁኖ የምወደው ልጅ ይሄ ነው ብሎ ሲመሰክርለት ሶስትነቱን በአንድ ድምፅ አንድነቱን አሳይቷል።

ኢኛ ኢትዮጵያውያን በልዩነት ውስጥ የፀና አንድነትን አፅንተን ባህላዊ እሴቶቻችን ጠብቀን ጠንካራ ሀገር የምንገነባው በልዩነት ውስጥ በተገነባ አንድነት ነው።

ከጥምቀት የምንማረው ይሄው ነው በሶስትነትና በአንድነት መካከል ምንም ልዩነት የለም። በኛ ውስጥም ያለው ይሄው ነው።

እናም ጥምቀትን ስናከብር ባለ ብዙ ፀጋ ባህል፣ ውብ ሕዝብ፣ ውብ ሀገር አለን ይችን ውድ ሀገራችን ልናለማት ልንጠብቃት በሁሉም የጋራ ጉዳዮቻችን በጋራ ቁመን ጠንካራ ሀገር በመስራት ለለልጆቻችን ማውረስን እያሰብን በዓሉን ልናከብር ይገባል።

መልካም የጥምቀት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ!!

Previous articleጥምቀት የነጻነት ቀን ነው።
Next article“ጥርን ናፍቀን፣ በጥር ደግሰን፣ በጥር የምናምር የመናገሻዋ ከተማ ነዋሪዎች ነን” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው